ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሜጋ ፕሮጀክቶችና ህዝብን ባሳተፉ የልማት ስራዎች የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል – ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

ግንቦት 12/2016 (አዲስ ዋልታ) በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሜጋ ፕሮጀክቶችና ህዝብን ባሳተፉ የልማት ስራዎች የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሙም በበጀት ዓመቱ ለማስመዝገብ የታቀደው የ7 ነጥብ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚሳካ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ በዘጠኝ ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማትና በሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በሪፎርም ስራዎች የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢኮኖሚ ልማት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ዓመታዊ ግቡ እንደሚሳካ ያሳዩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በሰብል ምርት ብቻ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት የ100 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መገኘቱን እና የሌማት ትሩፋት ትልቅ ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ በተደረገ የፖሊሲ ማሻሻያ እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግብዓት አቅርቦት፣ መሰረተ ልማትና የፋይናንስ ብድር በመሻሻሉ የዘርፉ ምርታማነት ወደ 56 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

በአገልግሎት ዘርፉ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትም ለኢኮኖሚ እድገቱ ትልቅ ሚና እንዳላቸው አውስተው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አፈጻጸሙም በጥሩ ሂደት መሆኑንና በዘጠኝ ወራት 4 ትሪሊየን ብር በዲጂታል የክፍያ ዘዴ መዘዋወሩን ጠቁመዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እና በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ኢኒሼቲቭ አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን በመገንባት ትልቅ ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትና የእድገት ምንጭ እንደሚሆን ጠቁመው ሀገራዊ የልማት ስራዎችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የህዝብ ተነሳሽነትና ተሳትፎ ማደጉንና በአረንጓዴ አሻራ፣ በትምህርት ቤት ማሻሻያ እና ሌሎች ስራዎች አይትኬ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።

ህዝቡን እና የግል ተቋማትን ባሳተፈ የማህበራዊ ልማት ስራም የበርካታ ዜጎችን ህይወት የሚያሻሽሉ የምገባ እና የቤት እድሳት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም ተቋማዊ አፈጻጸምን ለማሳደግና ማክሮ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

ለዚህም የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ የገቢ አሰባሰብን ማዘመን፣ ዲጂታላይዜሽንን ማስፋት፣ የሪፖርት የጥራት ደረጃን ማስጠበቅ፣ የስታቲስትክስ ፕሮግራምን መተግበርን ጨምሮ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን በውጤታማነት ለመምራትና የህዝቡን የመልካም አስታደደር ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስም ብቁ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር የመገንባት ስራ መጀመሩንና የመንግስትን የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ አፈጻጸምን በተያዘው እቅድ መሰረት ለማሳካትም የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለማሳያነትም የሱፐርቪዥን ቡድን በማቋቋም በክልሎችና በፌደራል ተቋማት የመስክ ምልከታ መደረጉን ጠቅሰዋል።