ብልጽግና ፓርቲ ከኅብረተሰቡ የተነሱ ችግሮችን ከስር መሠረታቸው ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚከተል አስታወቀ

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) ብልጽግና ፓርቲ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ውይይቶችን መሠረት በማድረግ ከኅብረተሰቡ እንደችግር የተነሱ ጉዳዮችን ከስር መሠረታቸው ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚከተል የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።
ፓርቲው በአገር ዐቀፍ ደረጃ በተካሄዱት ውይይቶች የተነሱ ሃሳቦችን በአግባቡ መዝግቧል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ እያንዳንዱ ጉዳዮች እንዴት እንደሚፈቱ ፓርቲው ተነጋግሮባቸዋል ብለዋል።
የውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ ጉዳዮች የተወሰኑት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸው ለእነዚህም ፈጣን ምላሽ ሰጪ እቅድ በማዘጋጀት ተግባራዊ እንደሚደረጉና አንዳንዶቹ ደግሞ የእቅድ አካል ሆነው በቀጣይ እየተፈቱ እንደሚሄዱ አስረድተዋል፡፡
ቀሪዎቹ በእቅድ መልክ ተካትተው በቀጣይ በትኩረት የሚፈጸሙ፣ አንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ በአካታች አገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ሆነው ውይይት ተደርጎባቸው የጋራ መግባባት ሊፈጠርባቸው የሚገቡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
እንደርሳቸው ማብራሪያ በእቅዱ ላይ በሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎች በአግባቡ ይታያሉ፣ ይፈታሉ፣ መፍትሄ ያገኛሉ፣ መቼ፤ እንዴትና በማን እንደሚፈጸሙ በግልጽ ይቀመጣል።
አካሄዱን የምንከተልበት አቅጣጫ በመቀመጡም ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
መድረኮቹ በጥቅሉ ሲታዩ በቀጣይ አገራዊ መግባባት ሊፈጠርባቸው የሚገቡ፣ በአካታች አገራዊ ምክክሩ እንደ አጀንዳ ተይዘው ምክክር የሚደረግባቸውና ለአገራዊ አካታች ምክክሩ ግብአት የሚሆኑ በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል ብለዋል።
ሕዝቡ በፓርቲውና በመንግሥት ትኩረት ይሻሉና መፈታት አለባቸው የሚላቸውን ጉዳዮች በነፃነት አንስቷል፤ የውይይት መድረኮቹ ከሌላው ጊዜ የተለየ አካሄድ የተከተሉ ነበሩ ሲሉም አክለዋል።
የአንዱ ክልል አመራር ሌላው ክልል ሄዶ ያወያየበት፣ በሚነሱት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች የተሻለ ግንዛቤ የተያዘበት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችል ነውም ብለዋል።