ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ጥቅምት 1 ይከበራል

መስከረም 29/2014 (ዋልታ) – ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ለ14ኛ ጊዜ በመላ አገሪቷ ይከበራል።

እለቱ “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ተነግሯል፡፡

ለብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ያለንን ቁርጠኝነት በሰንደቅ ዓላማችን ፊት ዳግም ቃላችንን እናድሳለን።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዋልታ በላከው መግለጫ ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፤ ዜጎች አገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና የስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀባረቅበት የአንድነትና ህብረት አርማና ምልክት መሆኑን ጠቅሷል።

በመሆኑም የፊታችን ሰኞ በሰንደቅ አላማችን ፊት ቀርበን ለብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ያለንን ቁርጠኝነት በሰንደቅ ዓላማችን ፊት ዳግም ቃላችንን እናድሳለን ብሏል።

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 ዓ/ም አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል።

ከብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ ሁለቱም አዋጆች (አዋጅ ቁ.654/2001 እና የተሻሻለው አዋጅ ቁ.863/2006ዓ/ም) በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 3 የተቀመጠውን የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ትርጓሜን መሰረት በማድረግ የወጡ ከመሆኑም በላይ ለብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሊሰጥ የሚገባውን ክብርና ትርጓሜ የሚያብራሩ አዋጆች ናቸው፡፡

በመሆኑም ይህን ዓላማ ለማሳካት የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በተለያየ መልኩ እየተከበረ እነሆ አስራ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

በዓሉ በተለይም በትምህርት ቤቶች ታዳጊ ተማሪዎች በጉጉት የሚጠብቁት መሆኑ፤ እንዲሁም ሁሉም ዜጎች እንደ ብሔራዊ በዓል የሚጓጉለትና እሴቶቹን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዲጠብቁት በየዓመቱ ትርጉም ባለው ሁኔታ በተጨማሪ ሁነቶች እያጀቡና እያደመቁ ማክበር አስፈላጊ ነው፡፡

በመሆኑም 14ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ መልዕክቶች ታጅቦ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡30 ሠዓት በፌዴራል፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ይከበራል፡፡

በዓሉ የሚከበረው በአንድ በኩል 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተካሂዶ በምርጫው ውጤት መሰረትም አዲስ ፓርላማ እና የመንግስት ምስረታ በተካሄደበት ማግስት እና በአገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባትና ብልፅግናን ለማምጣት አዲስ ምእራፍ በጀመርንበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው፡፡

የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እየተፈታተኑ ባሉበት በዚህ ወቅት መከበሩ ተናበንና ተደራጅተን በተባበረ ክንድ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመመከትና ለመቀልበስ በጋራ በቆምንበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሷል።

እለቱ በዓሉ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሪነት በመላው አገሪቱ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ መስተዳድሮች ፣ የመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ስነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ይሆናል፡፡