ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት

የካቲት 30/2015 (ዋልታ) ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ድርቅ ለመገምገም እና ምላሽ ለመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ስብሰባ ምክር ቤቱ የድርቁን ዝርዝር ሁኔታ፣ የደረሰውን የጉዳት መጠን፣ የተከናወኑ የአደጋ ምላሽ ሥራዎችን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን በሚገባ ገምግሟል።

ጥንካሬዎች እና ጉድለቶችም የተለዩ ሲሆን በአጭር እና በረጅም ጊዜ ሊከናወኑ የሚገባቸውን የአደጋ ምላሽ እና የዘላቂ ልማት ሥራዎች በመለየት በቅንጅት እና በርብርብ ለመተግበር አቅጣጫ ተቀምጧል።

በተለይም በመጪዎቹ አራት ወራት የሚሠሩ ሥራዎችን በመዘርዘር በቅርብ እየገመገመ ለመሥራት ወስኗል።

በዋነኛነት በአየር ሁኔታ መዛባት መንሥኤነት በተለይም ላለፉት አምስት የዝናብ ወቅቶች በተፈጠረው ከፍተኛ የዝናብ እጥረት የተነሣ በሀገራችን ደቡባዊ፣ ደቡብ ምሥራቃዊ እና ደቡብ ምዕራባዊ ክፍሎች ድርቅ ተከሥቶ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል።

የፌዴራል መንግሥት እና ክልሎች ከሕዝብ እና ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ለችግሩ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በሌላ አንጻር በሰው ሠራሽ አደጋዎች መንሥኤነት ተፈናቅልው የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረትን የጠየቀ ሥራ ሆኗል።