ተላላክ፣ ደዌና ዳሊፋጌ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል ወረራ ባደረገበት ወቅት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን በዚህም ክልሉ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ሆኖም የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባደረገው ርብርብ በአሁኑ ወቅት ተላላክ፣ ደዌና ዳሊፋጌ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በድጋሚ አግኝተዋል፡፡
ኤሌክትሪክ የማገናኘቱ ሥራ በከተሞቹ የመዘግየቱ ምክንያት ከሚሴ ሰብስቴሽን ላይ በትራንስፎርመር ላይ ባገጠመ ብልሽትና በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በከሚሴ ማዕከል ስር የሚገኙ የቦራ፣ ገርባና ኮርሽም ሳተላይቶች ላይ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት በማጋጠሙ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
በቀጣይም ቀሪ የጥገና ሥራዎች ተጠናቀው ሌሎች ከተሞችም የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያገኙ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል፡