ተመራጩ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ዛሬ በዓለ ሲመታቸውን ያከብራሉ

መስከረም 3/2015 (ዋልታ) አምስተኛው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዊሊያም ሩቶ ዛሬ በደማቅ ሁኔታ በዓለ ሲመታቸውን ያከብራሉ፡፡

በበዓለ ሲመቱ ላይ ከ20 በላይ ሀገራት መሪዎች እንደሚገኙ የኬንያው ጋዜጣ ቱኮ አስነብቧል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊኩ ፌሊክስ ተሸሰኬዲ፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ እና የሞዛምቢኩ ፊሊፕ ንዩሲ ናይሮቢ የደረሱ መሪዎች ናቸው፡፡

የምርጫውን ሂደት በታዛቢነት የተከታተሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በበዓለ ሲመቱ ላይ ለመታደም ኬንያ ተገኝተዋል፡፡

በዓለ ሲመቱ የሚከበርበት ስፍራ ከ60 ሺሕ በላይ ኬንያዊያንን እንዲያሳትፍ ተደርጎ መዘጋጀቱን የሀገሪቱ መንግሰት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በምርጫው የሩቶ ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ በበዓለ ሲመቱ ላይ እንደማይገኙ የኬንያ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡

ራይላ ኦዲንጋ  ምርጫውን እንዲያሸንፉ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በስፍራው ተገኝተው በትረ ስልጣኑን እንደሚያስረክቡም እየተጠበቀ ሲሆን መርሃ ግብሩ በሀገሪቱ ቴሌቪዥኖች በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል፡፡

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዊሊያም ሩቶን ፕሬዝዳንትነት ካጸደቀ በኋላ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኬንያታ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመራጩን ፕሬዝዳንት እንኳን ደስ ያለዎት ያሏቸው ሲሆን ትላንት በቤተመንግስት ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል፡፡

በዚህም ወቅት አዲሱ ፕሬዝዳንት ሁሉንም ኬንያዊያን ያለምንም ልዩነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል፡፡

በነስረዲን ኑሩ