ተቋሙ በ2013 ዓ.ም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ቁጠባ አሰባሰበ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ በ2013 ዓ.ም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ቁጠባ ማሰባሰብ መቻሉ ተገለጸ፡፡

ከተመሰረተ 24 ዓመታትን ያስቆጠረው ተቋሙ በዚህም ጥርቅም የቁጠባ አፈጻጸሙን (commulative saving) ከ36 ቢሊየን ብር በላይ አድርሷል፡፡

ተቋሙ ሲመሰረት  የነበረው ካፒታል አምስት መቶ ሺህ ሲሆን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ብዛትም አራት ብቻ እንደነበር ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይሁን እንጂ ባሁኑ ጊዜ የተቋሙ አጠቃላይ ሀብት 10 ነጥብ 7 ቢሊየን የደረሰ ሲሆን የካፒታል መጠኑም ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል፡፡

ተቋሙ ለዜጎች እየሰጠ ባለው አገልግሎት መነሻ ከአነስተኛ ቁጠባና ብድር ተነስተው ከፍተኛ ሀብትና ካፒታል በመፍጠር ወደ ባለሀብትነት የተሸጋገሩና ለበርካታ ዜጎች ሥራ ዕድል የፈጠሩ ደንበኞችን ያፈራ ነው፡፡