ነሀሴ 12/2013 (ዋልታ) – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የባህል ማዕከል በከፍተኛ ትምህርት በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ሚኒስቴሩ በስድስት ዩኒቨርስቲዎች የሰላም ትምህርት እንዲሰጥ የሚያስችል ስምምነት ከተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የባህል ማዕከል (UNISCO) ጋር በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተፈራርሟል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በዩኒቨርስቲዎች ከተለያዩ አካባቢዎችና ባህሎች የመጡ ተማሪዎች በመሆናቸዉ የሰላም ትምህርት በመስጠት ተማሪዎቹ እንዲወያዩና የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያመጡ የተግባር ስልጠና ይወሰዳሉ ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በሚማሩበት ጊዜ የማህበረሰብን የግጭት አፈታት መንገድና የሰላም ፋይዳውን የሚያትት ይሆናል ብለዋል።
የትምህርቱ ዋና አላማ ተማሪዎችን ወደ ሰላም የሚያነቃቃ፣ ሰላምን ለማምጣት፣ ግጭትን መከላከልና የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ሲሆን በ6 ዩኒቨርስቲዎች እንደመጀመርያ ለመስጠት ታስቧል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዉ ዉጤቱ እየታየና እየተጠና በሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም የሚሰጥ ይሆናል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዩኒቨርሲቲዎች በወጣቶች መካከል ማህበራዊ ትስስርንና ውይይትን ለመፍጠር ጥሩ መድረክ ናቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት አልፎ አልፎ የሚስተዋለዉን ግጭት ሊያቆሙና ለዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ብዝሃነት ምላሽ ሰጭ የከፍተኛ ትምህርት አከባቢን መፍጠር የሚያግዙ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በመግባቢያ ሰነዱ የፊርማ ስነስርዓት ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ፣ የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የባህል ማዕከል (UNISCO) ዳይሬክተር፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደርና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንትና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።