ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የውጭ ጣልቃገብነትን በመቃወም ለዓለም አቀፍ ተቋማት ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው – አቶ ሊላይ ኃይለማሪያም

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የውጭ ጣልቃገብነትን በመቃወም በመዲናዋ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው ሲሉ አቶ ሊላይ ኃይለማሪያም ተናገሩ።

የራዕይ ተጋሩ ኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ሊላይ ኃይለማሪያም ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ ሊላይ አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች መጠነ ሰፊ ወረራ ሲፈጸም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በዝምታ አልፎታል ይላሉ።

የጸጥታ አካላት በተቀናጀ መልኩ ወራሪውን የአሸባሪ ቡድን መመከት ሲጀምሩ ደግሞ ድምጻቸውን እያሰሙ መሆኑን ትዝብታቸውን ገልጸዋል።

እውነት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እጅ በመሆኑ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዲያውቅ ሳይታክቱ  መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች መቀመጫ መሆኗን አስታውሰው፤ ከዚህ አኳያ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ያልተገባ የውጭ ጫና ለእነዚህ ተቋማት ማሰማት አለባቸው ብለዋል።

ለዚህም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች በስፋት መሳተፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤትን በመጠቀም ሁሉም ጥቁሮች ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል ይላሉ።

ከዚህ ጎን ለጎን ሰፋፊ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን ያለማቋረጥ ማድረግ እንደሚገባም ነው አቶ ሊላይ የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ ቢቻል የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ሃሳብ ማስቀየር ቀላል እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የውጭ ጣልቃ ገብነቱ ጠንካራ ኢትዮጵያን ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው እንደሚገባም  አቶ ሊላይ ተናግረዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካዊ ከባቢያዊ ሁኔታ ላይ ትፅዕኖ ፈጣሪ እንዳትሆንና በጥቅሉ ጠንካራ አፍሪካን ማየት ስለማይፈልጉ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ነባራዊ ሁኔታውን በአግባቡ ተረድተው የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ጫና ለመመከት ሁለገብ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ራዕይ ተጋሩ ኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ንቅናቄ እስካሁን የተሻሉ የስራ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማህበሩ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የትግራይ ሕዝብና አሸባሪው ህወሓት አንድ የሚያደርጋቸው ምንም ነገር እንደሌለ ግንዛቤ በመፍጥር ላይ ይገኛል ብለዋል።

እንደ አቶ ሊላይ ገለጻ፤ በተሰራው ስራም ከወዲሁ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አብራርተዋል።