ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአዲሱ የመንግስት ካቢኔ መካተታቸው  ተጋግዘው መስራት የሚችሉበት እድል መኖሩን ማሳያ ነው – ኡስታዝ አቡበከር

መስከረም 30/2014 (ዋልታ) ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአዲሱ የመንግስት ካቢኔ መካተታቸው ከመገፋፋት ይልቅ በአገር ጉዳይ ላይ ተጋግዘው መስራት የሚችሉበት እድል መኖሩን ማሳያ ነው ሲሉ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ገለጹ፡፡
ኡስታዝ አቡበከር የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በአዲሱ የመንግስት ካቢኔ መካተታቸው ከመገፋፋት ይልቅ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አዲስ የፖለቲካችን አቅጣጫ መከተላቸውን የሚያሳይ መሆኑን ገልፀው፣ ይህም በአገር ጉዳይ አብሮ መስራት የሚችሉበት እድል እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ኡስታዝ አቡበከር ገለፃ፤ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በመንግስት ሹመት ውስጥ መካተታቸው ከመጠፋፋትና ከመገፋፋት ይልቅ በመተባበር ሀገርን መለወጥ የሚያስችል ትልቅ እድል እንዳለ ያሳየ ተግባር ነው፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ ላይ መሳተፋቸውና በአዲሱ የመንግስት ካቢኔ መካተታቸው በብዙ መልኩ ለአገር ይጠቅማል ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፣ የተለያየ ሀሳብ ያላቸውን ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ ላይ አብሮ መስራት አዲስ ባህል ትልቅ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው፤ ሀገሪቱ የተጋረጡባትን ችግሮች ለመፍታትም መሰረት ይጥላል ብለዋል።
በአገሩ ጉዳይ ሁሉም ዜጋ ባለድርሻ አካል መሆኑን የገለጹት ኡስታዝ አቡበከር፣ አዲሱ መንግስት ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በተለያዩ የካቢኔ ሹመቶች ውስጥ ማካተቱ ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘው የተነሱትን ሀሳብ ወደ ተግባር በመለወጥ ለቃላቸው ታማኝ መሆናቸውን ያሳዩበት እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢፕድ ዘግቧል።