ታሪክ የሀገር ግንባታ መሰረት ነው – የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

ሰኔ 18/2016 (አዲስ ዋልታ) ታሪክ የሀገር ግንባታ መሰረት ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር “ታሪክ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በሀገራችን ዛሬ ላይ ለሚስተዋሉት አለመግባባቶች ምክንያቱ ታሪክን በአግባቡ አለመያዛችን ነው ብለዋል፡፡

ታሪክ ከታሪክ ባለሙያዎች እጅ አፈትልኮ እየወጣ በጥቅም ፈላጊ ፖለቲከኞች እየተዘዋወረ ይገኛል ያሉት ሚንስትሩ የታሪክ ምሁራን ታሪክን ወደ ባለሙያዎቹ ሊመለሱ ይገባል ሲሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ያደጉት ሀገራት ለእድገት መሰረት የሆናቸው በአግባቡ የያዙት ታሪካቸው ነው፤ እኛም የገጠሙንን ፈተናዎች በማለፍ ሀገርን ወደ እድገት ጎዳና ለማሻገር እና ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለመፍጠር ታሪካችንን በአግባቡ እውነታውን ሳይለቅ አክብረን መያዝ አለብን ነው ያሉት፡፡

ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር)

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ታሪክን የማያውቅ ዜጋ መሰረት የለውም፤ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ መሰረት ታሪክ አይተኬ ሚና አለው፤ የወል ትርክት በመገንባት ሀገርን ማሳደግ ይገባናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች በትክክለኛ ታሪክ ግንባታ ላይ ለሀገር ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የሰላም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት