ትሕነግ ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን አንድ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ አጋለጠ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ለሌላ አውዳሚ ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሀይል እየመለመለ መሆኑን አንድ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ አጋለጠ።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በሚገባ ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ገልጿል።

አሸባሪው ትሕነግ ጠብ አጫሪነት በቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጉብኝት ያደረገው “የስኩፕ ኢንዲፔንደንት ዜና” ዋና ኤዲተር አላስቴየር ቶምሶን፤ የቡድኑ ዋነኛ ፍላጎት ዳግም ጦርነት መቀስቀስ መሆኑን አስረድቷል፡፡

የሽብር ቡድኑ ከዚህ ቀደም በርካቶችን በጦርነት በመማገድ ለሞት መዳረጉን አስታውሶ፤ ቡድኑ አሁንም ተመሳሳይ ተግባር ለመድገም እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ነው የተናገረው፡፡

ለዚህ ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተዋጊዎች እየመለመለና እያሰለጠነ መሆኑን በአስረጂነት አንስቷል፡፡

በጦርነቱ እጅግ ከተጎዳው የህብረተሰብ ክፍል ለዳግም ጦርነት ምልመላ ማካሄዱ አሳዛኝ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በሚገባ በመገንዘብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ጠቅሶ፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ውጤቱ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ነው የገለጸው፡፡

በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ባደረገው ጉብኝት በተለይ በወልቃይት ጠገዴና ጸለምት አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ የተጨፈጨፉ ዜጎችን ጅምላ መቃብር ስለመመልከቱ ተናግሯል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው ትሕነግ ባለፉት 40 ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈጽም የነበረውን ግፍ በጥናት አስደግፎ ይፋ ማድረጉን አስታውሶ በዚህም ዩኒቨርሲቲው በወልቃይት አካባቢ 20 የጅምላ መቃብሮችን ይፋ ማድረጉን እና ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ከተቻለ ሌሎች የጅምላ መቃብሮች ሊገኙ እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጅምላ ጭፍጨፋ ላይ ምርምር የሚያደረጉ ባለሙያዎችን በመጋበዝ በስፍራው ተጨማሪ ጥናቶችን ማከናወን እንደሚገባም ነው የጠቆመው፡፡