ትሕነግ ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ አለመውጣቱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ትሕነግ በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ከወረራቸው የአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወጥቻለሁ በማለት ከሰሞኑ ከእውነት የራቀ መረጃ እያሰራጨ ነው ሲል የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የሽብር ቡድኑ በአፋር የዘር ማጥፋት በመፈፀም፣ የአካል ጉዳት በማድረስ፣ ከቤት ንብረት በማፈናቀል እና የግለሰቦችና የሕዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ከባድ ዝርፊያ እና ውድመት ማድረሱ ይታወቃል ብሏል።

ቡድኑ እያካሄደ ያለው ጦርነት የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ወደ ሃይማኖት ጦርነት እንዲቀየር ቁርአን በማቃጠል፣ መስጂዶችን የማውደም ሙከራ አድርጓልም ነው ያለው።

ከዚያም አልፎ ለዘመናት አብረው የኖሩ የአፋር እና የትግራይ ሕዝብ በዘር እንዲጣሉና ጦርነቱ የብሔር ጦርነት እንዲሆን ብርቱ ጥረት ቡድኑ ቢያደርግም ይህ እኩይ ሀሳባቸው እንዳይሳካ የአፋር ሕዝብና መንግሥት ትልቅ ትግል አድርገዋል ብሏል።

ቡድኑ አሁንም ከአፋር ክልል ያልወጣ ሲሆን የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንቅስቃሴው እንደቀጠለ ነው ሲል አሳውቋል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

አሸባሪው ሕወሓት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ከወረራቸው በአፋር ክልል የኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወጥቻለሁ በማለት ከሰሞኑ ከእውነት የራቀ የሀሰት የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ ይገኛል።

በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በንፁሃን ላይ ከባድ ድበደባ በመፈፀም የኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎችን መጋሌ ወረዳ ፤አብአላ ወረዳ፤ አብአላ ከተማ አስተዳድር፤ኤረብቲ ወረዳ፤ በራህሌ ወረዳነና ኮነባ ወረዳን በሀይል በመቆጣጠር የዘር ማጥፋት በመፈፀም ፣ የአካል ጉዳት በማድረስ፣ ከቤት ንበረት በማፈናቀል እና የግለሰቦችና የህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ከባድ ዝርፊያ እና ውድመት ማድረሱ ይታወቃል።

ጁንታው እያካሄደ ያለው ጦርነት የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ወደ ሃይማኖት ጦርነት እንዲቀየር ቁርአን በማቃጠል፣ መስጂዶችን በማውደም ሙከራ አድርጓል። ከዚያም አልፎ ለዘመናት አብረው የኖሩ የአፋር እና የትግራይ ህዝብ በዘር እንዲጣሉና ጦርነቱ የብሄር ጦርነት እንዲሆን ብርቱ ጥረት ቡድኑ ቢያደርግም ይህ እኩይ ሀሳባቸው እንዳይሳካ የአፋር ህዝብና መንግስት ትልቅ ትግል አድርገዋል።

ቡድኑ በኪልበቲ ረሱ በቁጥጥሩ ስር ባደረጋቸው ወረዳዎች ለማሰብ የሚዘገንኑ እጅግ አረመኔያዊ የሆነ ጭካኔ የተሞላበት በከባድ መሳሪያ ንጹሀን ሴቶችን፤ ህጻናትና አዛውንቶችን በጅምላ በመጨፍጨፍ፤ ከ500 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ የከባድ መሳሪያውን ድብደባ በማጠናከር ለከባድ እንግልትና ስቃይ እንዲዳረጉ በማድረግ በሀብትና ንብረት ላይ የተቀናጀ የሆነ ዝርፊያና ውድመት በመፈፀም በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ፤ የንግድ ተቋማት ላይ፤ የሀይማኖት ተቋማት ላይ እንዲሁም የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተለይም በሆስፒታልና የጤና ተቋማት፤ በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ በውስጡ ያለውን ንብረት በሙሉ በመዝረፍና በማውደም መረጃዎችን በማጥፋት፣ በመጓጓዣ መጫን የሚፈልጉትን ጭኖ በመውሰድ፣ ያልፈለጉትን ደግሞ እልህ በተሞላበት ሁኔታ በማውደም አሸባሪው ህወሀት የአፋር ህዝብ ቀንደኛ ጠላትነቱን በማስመስከር አሁን ላይ ደግሞ “ከያዝናቸው አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለቅቀናል’ በማለት የተካነበትን ነጭ ውሸት እያሰራጨ ነው።

ይህ ቡድን የተካነበትን የማደናገሪያ የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቅቄያለሁ በማለት በሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይ በማራዘም ቀጠናውን አሁንም ወደ ቀድሞው ሰላምና መረጋጋት እንዳይመለስ እና ግጭቱ እንዳይቆም እንደዚሁም የሰብአዊ ድጋፍ በሚፈለገው መልኩ እንዳይደርስ እንቅፋት ለመሆን እና ርሃብን ለርካሽ ፖለቲካቸው ትርፍ መጠቀሚያ ማድረግ መቀጠሉ “ከአፋር ሙሉ በሙሉ ወጥተናል” ፕሮፖጋንዳቸው ማሳያ ነው። በመሆኑም የፌደራል መንግሥትም ሆነ ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ የዚህን እኩይ ቡድን ሴራ በቅጡ በመረዳት ቡድኑ የአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዲመለስ ቁርጠኛ አለመሆኑና ለዚህም ኃላፊነቱን አሸባሪው ሕወሓት የሚወሰድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የዓለም ኅብረተሰብ ጁንታው በአፋር ሕዝብ ላይ ያደረሰውን የዘር ማጥፋትና ግፍ እና በደል በአግባቡ እንዲገነዘብ ሰፊ ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን አመርቂ የሆኑ ውጤቶን በማስገኘትም ላይ ይገኛል።

ጁንታው በትግራይ ሕዝብ ላይ እየቆመረ ያለውን ቁማር በአፋር ሕዝብና መሬት ላይ ሆኖ እየፈፀመ ያለውን የፖለቲካ ንግድ የማያዛልቅ በመሆኑ ባስቸኳይ ሊያቆም ይገባዋል። የትግራይ ሕዝብም የሕወሓትን ሴራ በአግባቡ ተረድቶ ቆሜለታለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብን በሴራ እያሰቃየ እና ለፖለቲካ ትርፉ መጫወቻ እያደረገ መሆኑን በመረዳት ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ ስም እየሰራ ያለውን ርካሽ የፖለቲካ ንግድ እንዲያቆም በአንድ ድምፅ በቃህ ማለት ግድ ይለዋል። ለሽብር ቡድኑ ሕዝብ የቱንም ያህል ቢሞት እና ቢሰቃይ ጉዳዩ አለመሆኑን በአፋር ህዝብ ላይ ብቻም ሳይሆን በትግራይ ሕዝብም ላይ በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል። ታሪካዊው የአፋር ሕዝብ ጠላት አሸባሪው ሕወሓት በሕዝባችን ላይ ያደረሰው ግፍና በደል ወሰን የሌለው ሲሆን ቡድኑ ያደረሰው ኪሳራም ታሪክ ሆኖ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል።

አሸባሪው ሕወሓት እድሜውን ለማራዘም የአፋርን መሬት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በሀይል በመያዝ ከባድ የሆነ ሰብአዊ ና ቁሳዊ ኪሳራ እያደረሰ ያለ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሌላ ትርፍና ሌላ ማደናገሪያ በመፍጠር በሀይል ከወረሯቸው የአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ወረዳዎች “ሙሉ በሙሉ ለቀናል” በማለት እየነዛ ያለው የተለመደ ውሸት ከውሸትነት የማያልፍ እና ጁንታው እስካሁን ድረስ ከኪልበቲ ረሱ ወረዳዎች ከመጋሌ፤ ከበራህሌ፤ ከኮነባ፤ ከአብአላ ወረዳ፤ ከአብአላ ከተማ አስተዳድር አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ያልወጣ እና የአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ የቡድኑ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው።

መንግሥት ለሰብአዊ ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሕዝብ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ባለበት ሁኔታ ቡድኑም ለቀጠናው ሰላምና ለሰብአዊ ድጋፍ መሳለጥ አይነተኛ ሚናን ለመጫወት በሀይል ከወረራቸው የአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎች ቀሪ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በአስቸኳይ ለቅቆ ሊወጣ ይገባል።

ቀጠናው ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስና ሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ ከስጋት ነፃ በሆነ መልኩ እንዲቀጥል በከባድ መሳሪያ ንፁሀንን በመደብደብ የአፋርን ወሰን ጥሶ በመግባት ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰው አሸባሪው ቡድን አካባቢውን በሙሉ ለቅቆ መውጣት ይገባል።

በመጨረሻም ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ በአሸባሪው ሕወሓት የሚነሱ የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ጩኸት ሳይሆን በትክክል በተግባር መሬት ላይ ያለውን ሃቅ በመረዳት ሁሌም ከእውነትና ከሰብአዊነት ጎን ሊቆም ይገባል!

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

ሚያዝያ 19/2014

ሠመራ