ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – 1888 ስቱዲዮ የመጀመሪያውን የቴክኖሎጂ ምርቱ የሆነውን “ትሪዮጵያ” የተሰኘ መተግበሪያ በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
መተግበሪያው “በቴክኖሎጂ ዘርፍ የ1888 የአድዋ ድልን መድገም” በሚል በዘርፉ የተሰማሩ ጀማሪ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎችንና ድርጅቶችን ለመደግፍ በተቋቋመው 1888 ስቱዲዮ የለማ ነው።
ትሪዮጵያ የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎችና ሆቴሎችን መረጃ ለጉብኚዎች የሚሰጥ መተግበሪያ ነው።
1888EC ስቱዲዮ ለወጣት የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ሃሳቦቻቸውን የሚያበለፅጉበትና ወደ ንግድ የሚያስገቡበትን፣ የምክር አገልግሎት፣ የገንዘብ ድጋፍና የጥምር ንግድ ስርዓት በማመቻቸት በዘርፉ ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን ለመፍጠር የተቋቋመ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ ተቋማቸው እንዲህ ያሉ በዘርፉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚሰሩ ተቋማትን እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
የ1888EC መስራች አቶ ሰለሞን ካሳ ለቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና በድህነትና ኋላቀርነት ላይ አዲሱን ትውልድ ለማዝመት ስቱዲዮው መቋቋሙን ተናግረዋል።
የ1888EC የመጀመሪያ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው ትሪዮጵያ መተግበሪያም የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅና ጎብኚዎችን ከሆቴሎች ጋር በማገናኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ የዘመኑ ጋሻና ጦራችን በቴክኖሎጂና በዲጂታል ክህሎት የተገነባ የሰው ሃይል መሆን አለበት ብለዋል።
አድዋ ላይ ተባብረን ድል እንዳደረግነው ሁሉ በቴክኖሎጂው ዘርፍም በትብብር በመስራት የራሳችንን የድል ታሪክ ማስመዝገብ አለብን ማለታቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
1888EC ለቴክኖሎጂ የስራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታን በማመቻቸት በዘርፉ የስራ እድል መፍጠር፣ ወጣት የስራ ፈጣሪዎችን ቁጥር ማሳደግና የዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባት የሚል ግብ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለ ስቱዲዮ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።