ትራንስፎርመሮችን የዘረፉ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳ ማሊማ ወረዳ ሌመን ከተማ ልዩ ስሙ አዋሽ አቡ ጉቱ በሚባል አካባቢ ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚሰጥ ባለ 50 ኬ.ቪ.ኤ ትራንስፎርመር እንዲሁም በዞኑ ሰበታ አዋስ ወረዳ አለምገና ከተማ አከባቢ ባለ 100 ኬ.ቪ.ኤ ትራንስፎርመር ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ግለሰቦቹን ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጾ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ታጠቅ አካባቢ ለኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት የሚሰጡ 3 ባለ 50 ኬ.ቪ.ኤ ትራንስፎርመሮች ላይ የስርቆት ወንጀል ሙከራ ሲደረግ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ንብረቱን ማዳን ተችሏል ብሏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም ከ2014 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በሰበታ፣ ዓለምገና፣ ቢሾፍቱ፣ ሌማን፣ ገላን እና ቡራዩ ከተሞችና አካባቢዎቻቸው ከ18 በላይ ትራንስፎርመሮች እና ከ400 ሺሕ ሜትር በላይ የኤሌክትሪክ ሽቦ ላይ የስርቆት ወንጀል በመፈፀሙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲስተጓጉል እና ተቋሙም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማጣቱን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችና ንብረቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የተደራጀ የስርቆትና ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ለኤሌክትሪክ መቆራረጥ ዋነኛ መንስኤ ከመሆኑም በተጨማሪ በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷልም ነው የተባለው፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW