ትኩረታችንን የከተማችንን ጸጥታ ከማስጠበቅ ሳንነቅል መደበኛ ስራችንን እናስከዳለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) ትኩረታችንን የከተማችንን ጸጥታ ከማስጠበቅና ከሀገራዊ የኅልውና ዘመቻው ላይ ሳንነቅል መደበኛ ስራችንን የምናስኬድ ይሆናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
የአዲስ አበባ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት የ2014 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸሙን የገመገመ ሲሆን በዚህም በሩብ ዓመቱ ለ350 ሺሕ ነዋሪዎች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዶ ለ55 ሺሕ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስታውቋል፡፡
ሀገር በኅልውና ዘመቻ ውስጥ ባለችበት ወቅት ወጣቶችና የከተማዋ ሴቶች ሲያነሱ የነበረው የስራ እድል ይፈጠርልን ሳይሆን ተደራጅተው የከተማዋን ጸጥታ ለማስጠበቅና በኅልውና ዘመቻ ውስጥ ግንባር ለመዝመት የሚቻልበት እድል እንዲመቻችላቸው እንደነበር ከንቲባ አዳነች አስረድተዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ ላይ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ሆነን በከተማ ግብርና፣ በአነስተኛና ጥቃቅን እንዲሁም በኢንዱስትሪ ልማት መስክ እና በተለያዩ ዘርፎች ለ55 ሺሕ የከተማው ነዋሪዎች የሥራ እድል በመፍጠር የዕቅዱን 35 በመቶ ማሳካት መቻሉ አመርቂ እንደሆነ መናገራቸውን የከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡
ወጣቶችና ሴቶች ከስራ እድል ፈጠራው ጎን ለጎንም የከተማዋን ጸጥታ ለማስጠበቅ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክረው ሊያስቀጥሉ ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ እስክትመለስ ሀገር ለማዳን እየተዋደቀ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ወጣቱ በማንኛውም መልኩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የፋይናንስ ድጋፍና የመሬት አቅርቦትን በተመለከተ አዲስ ብድርና ባለድርሻ ተቋማት በቅንጅት ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት ከንቲባዋ በየትኛውም መንገድ የተወሰደ የስራ ማስኬጃ ብድር የሕዝብ ሀብት በመሆኑ በጊዜው ተመልሶ ለሌላ አዲስ ስራ ፈላጊዎች መዘዋወር እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡