“ትግሉ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ከአማራ ክልል የማስወጣት ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የምንቀብርበት ነው” – አቶ አገኘሁ ተሻገር

ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ በጥሩ ብርሃን መሠረታዊ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ያሰለጠናቸውን የልዩ ኀይል ምልምል የፖሊስ ሰልጣኞችን ዛሬ አስመርቋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከፍጥረቱ ጀምሮ አማራን በጠላትነት የፈረጀ ጸረ ሕዝብ ቡድን ነው ብለዋል።
አማራን በጠላትነት በመፈረጅም ባለፉት አርባ ዓመታት የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጣሊያን ከፈጸመው በላይ አንደሆነ ገልጸዋል።
በሌሎች ሕዝቦችም በጠላትነት እንዲታይ ያደረገ አሸባሪ ቡድን መሆኑን አንስተዋል።
በአገዛዝ ዘመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማራዎችን ባደራጀው ቡድን እንዲፈናቀሉ እና ንብረታቸው እንዲወድም አድርጓል ብለዋል።
የወልቃይት እና የራያ አካባቢዎችን በጉልበት ወደ ራሱ በመከለል መሬታቸውን ነጥቋል፤ በርካታ አማራዎችን በጅምላ መገድሉንም አንስተዋል።
በባንዳነት የሚታወቀው ይህን ከፋፋይ መሰሪ ቡድን ዛሬም የፈጸመው ወረራ እና ዘረፋ የቀደመው ግብሩ መገለጫ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ይህ ወራሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ኀይሎች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ባንዳነቱን አሳይቷል ብለዋል ርዕሰ መሥተዳድሩ።
ከግብጽና ሱዳን ጋር በመሰለፍ የአባይ ግድብን ለማሰናከል ጥሯል ነው ያሉት።
የትህነግን ወረራ ለመመከትም ክልሉ ባስተላለፈው የክተት ጥሪ በርካታ ወጣቶች ልዩ ኀይሉን በመቀላቀል አሽባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን በወኔ እየታገሉት እንደሚገኙ ገልጸዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ ትግሉ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ከአማራ ክልል የማስወጣት ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የምንቀብርበትም ነው ብለዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።
ዛሬ የተመረቁ ምልምል የልዩ ኀይል አባላትም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች ክልሎች ልዩ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት በአማራ ብሎም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በመመከት ታሪካዊ አደራ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።