ቻይና ጭቆናን አትቀበልም – ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ

ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ

ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – ቻይና ሌሎች አገሮችን አትጨቁንም ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ሺ ጂንፒንግ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ 100ኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ በዓል ላይ ባሰሙት ንግግር ላይ ገለጹ፡፡

በመታሰቢያ በዓል ሥነ ሥርዓት ላይ ወታደራዊ የአውሮፕላን ትርኢቶች፣ የመድፍ ሰላምታዎች እና የአርበኞች ዘፈኖች ተሰምተዋል፡፡

ሀገሪቱ ላለፉት ሳምንታት በፓርቲው ፀድቆ የታተመውን የቻይና ታሪክ በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡

ፕሬዘዳንት ሺ ጂንፒንግ ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው ንግግራቸው ፓርቲው በዘመናዊ ቻይና ውስጥ ያለው ሚና ለአገሪቱ እድገት ማዕከላዊ እንደነበረና ፓርቲውን ከሕዝብ ለመነጠል የሚደረግ ሙከራም ‹‹እንደማይሳካ›› ተናግረዋል፡፡

ቻይናን ማዳን የሚችለው ሶሻሊዝም ብቻ ሲሆን፣ ቻይናን ሊያለማ የሚችለው በቻይና መልክ የተቀረፀ ሶሻሊዝም ብቻ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም “ማንም ሰው ቻይናን እንዲገደብ፣ እንዲጨቁን ወይም እንዲገዛ በጭራሽ አንፈቅድም” ብለዋል፡፡

‹‹ይህንን ለማድረግ የሚደፍር ማንኛውም ሰው ከ1.4 ቢሊየን በላይ የቻይና ህዝብ በተሰራው ታላቁ የብረት ግንብ ጋር ጭንቅላቱን ያፋጥጣል›› ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት በተለይ በታይዋን ጉዳይ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የምትከተለው ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር ብታይም ቤጂንግ ደሴቲቱን እንደ አንድ አውራጃ ትመለከታለች፡፡

ቤጂንግ ደሴቲቱን ለመመለስ ኃይል የምትጠቀም ከሆነ የአሜሪካ ሕግ ታይዋን ራሷን ለመከላከል ድጋፍ እንድታደርግ ያስገድዳል፡፡ ፕሬዘዳንቱ ቻይና ከታይዋን ጋር ለመዋሃድ ‹‹የማይናወጥ ቁርጠኝነቷን›› ይዛ እንደቀጠለች ተናግረዋል፡፡

‹‹የቻይና ሕዝብ ብሔራዊ ሉዓላዊነቱን እና የግዛት አንድነቱን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት፣ ፍላጎት እና ችሎታ ማንም አቅልሎ መመልከት የለበትም›› ብለዋል፡፡

ሆንግ ኮንግም በተመሳሳይ ቀን ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ለቻይና ተላልፋ የተሰጠችበትን በዓል እያከበረች ነው፡፡