ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የተናገሩት በሮቤ ከተማ በአረብ ኤሜሬት ዓለም ዐቀፍ ቀይ ጨረቃ ማኅበር ድጋፍ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ባስመረቁበት ወቅት ነው።

ከ147 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶቹ በአከባቢው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እና መነቃቃትን የሚያመጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

መንግሥት የሕዝብ ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

ገቢን እና የዜግነት አገልግሎትን በማሳደግ እንዲሁም ከድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባባር በክልሉ ለውጥ ማምጣት ተችሏልም ብለዋል።

የማኅበሩ ዋና ፀኃፊ ፋሀድ አብዱረህማን ማኅበራቸው በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ሰርቶ ያላደገ ሀገር የለም ያሉት ዋና ፀኃፊው ኢትዮጵያዊያንም ለሀገራቸው እድገት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሚልኪያስ አዱኛ (ከሮቤ)