ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ 577 የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት ላይ እርምጃ ተወሰደ

መጋቢት 13 ቀን 2013 (ዋልታ) ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 577 አመራርና አባላት ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱን የብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ኢስሃቅ አብዱልቃድር እንደገለጹት ፓርቲው በቅርቡ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ባካሄደው አንደኛ ጉባኤ በክልሉ ጥልቅ ግምገማ አድርጎ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮችና አባላት ላይ ከኃላፊነት እንዲነሱ ከማድረግ ጀምሮ የተለያየ እርምጃዎችን ወስዷል።
በግምገማውም ከቀበሌ ጀምሮ በወረዳ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 577 የፓርቲው አመራርና አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡
አመራርና አባላቱ ላይ እርምጃ የተወሰደው በክልሉ ከፓርቲው መተዳደሪያ መሠረት የሆነውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ከማስጠበቅ ይልቅ የሕዝብን ጥቅም በመጻረር መንቀሳቀሳቸው እንደሆነ ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ከኃላፊነት ማንሳት፣ በከባድ እና ቀላል ማስጠንቀቂያ፣ ሙሉ በሙሉ ከአመራርነት ተነስተው ባለሙያ ሆነው እንዲሰሩ የተመደቡ መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
የፓርቲውን መዋቅር የማጥራት እርምጃው በዚህ እንደማያበቃ እና በተከታታይ ጠንካራ ግምገማዎች እንደሚቀጥልም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በክልሉ በጥፋት ተላላኪዎች የሚፈጸመውን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ማቆም እና የኑሮ ውድነቱን ማስቀረት ቀጣይ ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡