ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የከተማዋ ፖሊስ ጥሪ አቀረበ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር የተለያዩ የጸጥታ ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል።

በተለይም ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከኅብረተሰቡ ጋር ባካሄደው ተግባራት የተለያዩ አጀንዳ ያነገቡ አካላት የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ ያደረጉትን ጥረት ለማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።

ለአብነትም በመዲናዋ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ድምጽ አልባ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ገንዘቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።

ለዚህም ኅብረተሰቡ ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ የአካባቢው ሰላምን ለማስጠበቅ ከጸጥታ አካላቱ ጋር ያደረገው ዘርፈ-ብዙ ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ መሆኑን ገልጸው ይህንን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ጸጥታን የሚያደፈርሱ የተለያዩ ጉዳዮችን በንቃት እንዲከታተልም ጥሪ አቅርበዋል።
በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ኅብረተሰቡን ለማሸበር ከሚነዙ የተለያዩ መረጃዎች ኅብረተሰቡ እራሱን እንዲጠብቅም ተናግረዋል፡፡

በዚህም መዲናዋን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ አጀንዳ ያነገቡ አካላትን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም ሰፊ እድል እንደፈጠረለትም ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW