ኅብረተሰቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት፣ ፓርቲውና ሕዝቡ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) ኅብረተሰቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት፣ ፓርቲውና ሕዝቡ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሞገስ ባልቻ በተለይ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የብልጽግና ፓርቲ በመላ ኢትዮጵያ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውሰው በመድረኮቹም ሕዝቡ ለመንግሥትና ለፓርቲው ግብዓት የሚላቸውን ሃሳቦች ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ዓላማም ፓርቲው ውይይት ያሳለፋው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች የሕዝቡን ጥቅም የሚያስከብሩና ፍላጎቱን ያገናዘቡ እንዲሁም ለሕዝቡ ወቅታዊ ጥያቄዎች ያለውን ግንኙነት ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕዝቡ ያለውን ሚና ለመገንዘብና የሕዝቡን ጥያቄዎች በማወቅ ለቀጣይ ተግባራዊ ሥራ ለመዘጋጀት መሆኑን ገልጸው መድረኮቹ ትልቅ ሕዝባዊ ተሳትፎ የነበራቸውና ሃሳቦች በነጻነት የቀረቡባቸው እንደሆኑ አመላክቷል፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ መድረኮች መዘጋጀት እንዳለባቸው የታየበት ነው ብለዋል፡፡
የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ሁሉም ጋር እንዲደርሱ ብሎም ውጤታማ እንዲሆኑ መፈለግ፣ አዳዲስ የመልማት ፍላጎት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦትና የኅብረተሰቡ ደኅንነት፣ የአመራር ተልዕኮ መዛነፍ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ ሌብነትና በአጠቃላይ የሕዝቡን እርካታ አላረጋገጡም የተባሉ ጉዳዮች በውይይቱ መነሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡
መንሥስት ኅብረተሰቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ጉባዔው ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ በማድረግ አመራሩ ያለምንም ልዩነት በአጭር ጊዜ የሚፈቱትን ችግሮች ገቢራዊ ማድረግ እንዳለበት፣ በዕቅድ የተያዙትንና ያልተያዙትን በመከለስ ውጤታማ ሥራ ለመስራት የሚያስችሉ መንገዶችና የሚፈቱበት ጊዜ መለየቱንም ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው አመራርና አባላት ተገልጋዩ በየደረጃው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ግንባር ቀደም ሆኖ በመፈፀም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል ችግሮች በሌላ አካል እንዲፈቱ ከመጠበቅ ይልቅ ኃላፊነቱን ታሳቢ ያደረገ ተግባር መፈፀም እንዳለበት እንዲሁም ሕዝቡ በመንግሥት የሚመጡ የመፍትሔ ሃሳቦች እንዳይደናቀፉ የራሱን ሚና መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
በተስፋዬ አባተ