ነዋሪዎቹ አሸባሪው የህወሐት ቡድን በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ በፅኑ እንደሚቃወሙ ገለጹ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የህወሐት ቡድን በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ በፅኑ እንቃወማለን ሲሉ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ።

ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

ከዞኑ 24 ወረዳዎችና ከተሞች የተወጣጡ  በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና አሸባሪውን ቡድን የሚያወግዝ  ሰላማዊ  ሰልፍ በሐረማያ ከተማ እያካሄዱ ነው።

ሰልፈኞቹ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ክብርና ፍቅር  በዚሁ ሰልፍ ላይ እየገለጹ ይገኛሉ።

አሸባሪው የህወሐት ቡድን በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ በፅኑ እንቃወማለን፣ እኛ የዞኑ ነዋሪዎች ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ነን፣ ክብርና ሞገስ ውድ ህይወታቸውን ለሰጡ መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላማችንን በማስጠበቅ ልማታችንን እናረጋግጣል እና መሰል  መልዕክቶች በሰልፉ ላይ  ተሰምተዋል፡፡

የህልውናችን መሠረት የሆነው የህዳሴ ግድባችን ግንባታን እስከመጨረሻው በመደገፍ ከዳር እናደርሳለንም ብለዋል።

በሰልፉ ወጣቶች፣ሴቶች፣አርሶ አደሮች፣የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል::