ነጻነት እና እኩልነት ፖርቲ መተዳደሪያ ደንብ ላይ መሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ

መጋቢት 18/2014 (ዋልታ) ከተመሰረተ ሶስት ዓመታት ያስቆጠረው ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ላይ መሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው እለት እያካሄደ ይገኛል፡፡
መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የፓርቲው መስራች ጉባኤ ላይ የጸደቀው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በሥራ ላይ በዋለባቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት በተግባር የተገኙ ልምዶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና መተዳደሪያ ደንቡን ከአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 74 ጋር ለማቀናጀት ሲባል ደንቡ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሲሳይ ነጋሽ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲው ጠቅላላ አባላት ቁጥር፣ ፓርቲው ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚፈጥረው ጥምረት እንዲሁም በአገር ዐቀፍ እና አካባቢ ምርጫዎች የፓርቲው እጩዎች የአመራረጥ ሥርዓት በመተዳደሪያ ደንቡ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የፓርቲውን ጠንካራ ጎኖች ለማዳበርና የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 74 መሰረት በደንቡ ውስጥ እንዲካተቱ እና እንዲስተካከሉ የተጠየቁት አንቀጾችም ጭምር ማሻሻያ እንደተደረገባቸዉ የፓርቲ ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
በጉባኤው የጎደሉ የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት