አለም አቀፍ ይዘት ያለው ጫና የተጋረጠበትን የአትዮጵያ አየር መንገድ ድምጽ መሆን

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) በአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን የቴሌቪዝን ጣቢያ አየር መንገዱ የጦር መሳሪያ ማመላለሻነት ውሏል በሚል የተሰራጨው ዘገባ አየር መንገዱን የምዕራባውያን ጫና ማሳረፊያ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ የቢዝነስና ምጣኔ ሀብት ዘርፍ የአቬሽን ዘጋቢ የሆኑት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ በቀለ ለዋልታ ቴሌቪዠን ገልጸዋል፡፡
አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ላይ የሚያበረክተው የውጭ ምንዛሬ መጠን በዓመት ከ4 ቢለዮን የአሜሪካ ዶላር የበለጠ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያን ከተቀረው አለም ጋር የማስተሳሰሩን ተግባር የሚወጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ተቋሙ ከራሱ አልፎ የሌሎች አፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን በመርዳትም በስኬታማነቱ የሚታወቅ ነው ይላሉ፡፡
አትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግሮችን በመመልከት አለም አቀፍ ጫናዎች በተበራከቱበት በዚህ ጊዜ ላይ የኢትዮጵያዊያን የአይን ብሌን የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጫናቸው ክንድ ማሳረፊያ ለማድረግ የሚፈለግ ያደርገዋል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ለዚህም መገለጫ ላለፉት ወራት በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ የሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ኒማ ኢልባግር የተዛባ ዘገባ ጠቋሚ ነው ብለዋል፡፡
ስለኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማነት ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው ጋዜጠኞች በሚገኙበት የሲ.ኤን.ኤን ተቋም የተዛባ ዘገባ መሰራጨቱ ተቋሙ የአንድ ወገን ተልዕኮ ማስፈጸሚያ እየሆነ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አለም አቀፍ ይዘት ያለው ጫና በመሆኑ ይህን ለመመከት እንዲቻል ለአትዮጵያ አየር መንገድ ድምጽ መሆን እንደሚያሰፈልግ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ በቀለ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሰለሞን በየነ