ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለልዩ ልዩ አገልግሎት እንዲውል የተሰጠውን መሬት አልሚዎች በአፋጣኝ አልምተው ለተፈለገው ዓላማ ማዋል ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ካለው እድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ ለመጣው የመሬት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት 138 ሄክታር (1.38 ሚ.ካሬ) ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲውል ለአልሚዎች አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህወጦች ተይዞ የነበረውን መሬት ወደ መሬት ባንክ በማስገባት ለረጅም ጊዜያት ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ እና ለከተማዋ እድገት እጅግ የሚያስፈልጉ ተቋማት እንዲኖራት ለማስቻል አልሚዎችን በግልጽ መስፈርት በመለየት በልዩ ሁኔታ መሬት እንዲሰጥ በካቢኔ መወሰኑን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መሬቱነረ ለመስጠት ሲወስን አልሚዎች የተሰጣቸውን መሬት አልምተው ለተፈለገው ልማት እንዲያውሉት እምነት ስላለው ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ አልሚዎች በአፋጣኝ ወደ ልማት መግባት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩም በመሬት እና መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋለውን የመሬት ወረራ እና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችና ማነቆዎችን በመፍታት፣ በህገወጥ የተያዘውን መሬት ወደ መሬት ባንክ በማስገባት፣ 430 በሚሆኑ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
ለልማት የሚውል መሬት የተሰጣቸው ተቋማት እና ልዩ ልዩ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ለዘመናት ታጥረው የነበሩ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ በማስገባት በግልጽ መስፈርት ለተቋማት እና ድርጅቶች እንዲተላለፍ መደረጉ ከተማ አስተዳደሩ ለግልጸኝነት፣ ለተጠያቂነት እና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩም በሰጣቸው መሬት ለተፈለገው ልማት እንዲውል በአፋጣኝ ወደ ስራ እንደሚገቡም የተቋማት እና ልዩ ልዩ ድርጅት ተወካዮች ቃል ገብተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በወሠነው መሠረት፡-
-ለተለያዩ ለእምነት ተቋማት 54 ቦታዎች (121 ሺህ 700 ካሬሜትር)
-ለአስር መንግስታዊ ላልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የመስሪያና ማስፋፊያ ቦታ የመሬት ጥያቄ የሚሰጡትን ማህበራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ30ሺህ 724 በላይ ካሬሜትር
-ለ44 አዲስ የኢንዱስትሪ ግንባታ እና 15 ነባር ኢንዱስትሪ ቦታ ማስፋፊያ ኢንዱስትሪዎች ከ537 ሺህ 834 በላይ ካሬሜትር
-ለአዳዲስ እና የማስፋፊያ የሆቴል እና የንግድ ማዕከላት ከ200 ሺህ 874 በላይ ካሬሜትር
-ከተማዋን የጤና ቱሪዝም ለማድረግ 13 ትላልቅ ሆስፒታሎችን ለመገንባት አስፈላጊ የመሬት ዝግጅት መደረጉ
-ለሮሃ የህክምና ማዕከል እና ለኢጋድ የካንሰር ልህቀት ማዕከል መገንቢያ መሬት ተሰጥቶ የግንባታ መሠረተ ድንጋይ መቀመጡን እና ለአፍሪካ ህብረት 939 ካሬሜትር ቦታ እንዲሰጥ መወሰኑን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።