መስከረም 14/2017 (አዲስ ዋልታ) ሀገራዊ የመሻገር ትልሞችን በታላቅ ርብርብና ቅንጅት በማሳካት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ የአገልጋይ አመራር ሰብዕናን ተላብሶ በውጤታማነት እንዲሰራ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።
ብልፅግና ፓርቲ ላለፉት 12 ቀናት በአዳማ ያካሄደው የከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ ተጠናቋል።
ፓርቲው “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ከ2000 በላይ ከፍተኛ የአመራር አባላቱ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ብልፅግና በማረጋገጥ የትውልዱን መፃኢ እድል ምቹና ስኬታማ ማድረግ በሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ሀሳቦች ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።
የአመራር አባላቱ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የህዝብ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት በተግባር አንድነት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በስልጠናው በቂ አቅም ያገኙበትና የነገዋን ኢትዮጵያ መስራት የሚያስችል ግንዛቤ የጨበጡበት እንደነበረ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ስልጠናው ሀገር ቀያሪም፣ ሀብት ፈጣሪም ሰው በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ ከተሞችና የፌዴራል ተቋማት ያለው ከፍተኛ አመራር በተመሳሳይ የፓርቲው ተልዕኮዎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ውጤት እንደሚያተጋው አብራርተዋል።
መሪነት ራስን መስጠትን፣ ሆደሰፊነትንና ዓላማን የማሳካት ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፣ ከፍተኛ አመራሩ የወሰደው ስልጠናም የመሪነት ቁልፍ መርሆዎችና ባህሪያትን በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደረገ በመሆኑ ፈጣንና እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ አቅም ይፈጠራል ሲሉ መግለጻቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመlaክታል።
በስልጠናው ህልምንና ትልምን ለማሳካት የሚያግዙ እይታዎችና የመፈፀሚያ ትርክቶች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች፣ በህዝብ ቅቡልነትና ትብብር የመስራት አቅም፣ እውቀት መር ሽግግርን ለማፅናት የሚያስፈልጉ ሰብዕናዎች ላይ የመስራትና የፀጥታ ችግሮችን ወደ ተሟላ ሰላም የሚያሻግሩ ሂደቶችና የአመራር ስነምግባርን በሚመለከቱና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።