አመራሩና ህዝቡ ሙሉ አቅሙን ኢትዮጵያን ማዳን ላይ ማድረግ አለበት- የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ

ጥቅምት 23/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሀመድ በወቅታዊ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ላይ እንደገለጹት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያግዙትን የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ተላላኪዎቹን አስተባብሮ በሁሉም አቅጣጫ ውጊያ ከፍቶብናል።

በሀገር ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከትም ህዝብና መንግስት ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሀረሪ ክልልም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ነዋሪው በተለያየ መልኩ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም አመራሩና ህዝቡ የህልውና ጦርነቱን ውስብስብ ባህሪ በመገንዘብ ሙሉ ትኩረቱንና አቅሙን ኢትዮጵያን በማዳንና የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ ላይ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የተደቀነብንን ሀገር የማፍረስ አደጋ ለመቀልበስ ሁሉም አመራር ተቀናጅቶ፣ ተናቦ እና የተግባር አንድነት ፈጥሮ ሀገርን ከብተና ክፉ ምኞት መታደግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

መላው የክልሉ ነዋሪዎች እና የፓርቲው አባላትም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እና ሌሎች የጸጥታ አካላትን በሞራል እና በሎጅስቲክ የመደገፍ ተግባሩን ማጠናከር አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ወጣቶችም እንደከዚህ ቀደሙ የመከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሀገር ማስቀጠልና ለውጥ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን ከማፍረስ ሰይጣናዊ ሕልማቸው ጋር አብሮ ለመቅበር ከመቼውም በላይ አንድነትን በማጠናከር ከጀግናው የመከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጎን መቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የአሸባሪውን ተላላኪዎች በተደራጀ መንገድ በማጋለጥ የአካባቢን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ እንዲሁም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በትኩረት መሰራት እንደሚገባም አቶ አብዱጀባር አስገንዝበዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲም ዛሬም በየግንባሩ በጽናትና በጀግንነት እየተፋለሙ ለሚገኙት የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጠንካራ ደጀን ከመሆን ባሻገር አመራሩንና ህዝቡን በማስተባበር በግንባር በመሰለፍ ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አቶ አብዱጀባር አረጋግጠዋል።