አሜሪካ ሚሳኤል ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቧን በመካከለኛው ምስራቅ አሰማራች

ነሐሴ 6/2016 (አዲስ ዋልታ) በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና የተባባሰውን ውጥረት ተከትሎ አሜሪካ ሚሳኤል ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቧን ልካለች።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ጸሐፊ ሎይድ ኦስቲን የተዋጊ ጄቶች ተሸካሚ መርከብም ወደ አካባቢው መላኩን ተናግረዋል።

አሜሪካ ይህንን እርምጃ የወሰደችው በቅርቡ የሐማስ እና የሂዝቦላ ከፍተኛ አመራሮች ከተገደሉ በኋላ ሰፋ ያለ ቀጣናዊ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት መስፈኑን ተከትሎ ነው።

በቴህራን የሐማስ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ከተገደሉ በኋላ ኢራን እስራኤልን እቀጣለሁ ማለቷን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል፡፡

እስራኤልን ከኢራን ከሚደርስባት ጥቃት ለመከላከል አሜሪካ ቁርጠኛ ናት ያሉት ጸሀፊው ሎይድ ኦስቲን “አሜሪካ አጋሯን ለመደገፍ የሚቻለውን እርምጃ ሁሉ ትወስዳለችም” ብለዋል።

የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት (ፔንታጎን) ባወጣው መግለጫ ሚሳኤል ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከብ እና ቀድሞ በቦታው የነበረ ሌላ መርከብን የሚተካ ኤፍ-35ሲ የተባሉ ተዋጊ ጄቶችን ተሸካሚ መርከብ ወደ ቀጣናው መላኩን አስታውቋል።

እስካሁን ድረስ ኢራን ምን ለማድረግ እንዳቀደች በግልጽ ያሳወቀችው ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል በኢራን ይደገፋል የሚባለው ሂዝቦላ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት ሰፍኗል፡፡

በእስራኤል ለተፈጸመው የሂዝቦላ ከፍተኛ አዛዥ ፉአድ ሹክር ግድያ ታጣቂ ቡድኑ ምላሽ እሰጣለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡