አሜሪካ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም እንዲመጣ ቁርጠኛ መሆኗን ገለፀች

አንቶኒ ብሊንከን

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቢሯቸው በኩል በኢትዮጵያ ግጭቶችን ለማስቆም እየተካሄዱ የሚገኙ ተግባራዊ ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሸባሪው ሕወሓት በፈጠረው ጦርነትና በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ ግጭቶች የተነሳ ብዙኃን ለችግር መጋለጣቸውን ያስታወሰው መግለጫው ይህንን ችግር ለመቅረፍ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተወሰደውን እርምጃ አድንቋል።

በተለይም በትግራይና አፋር ክልሎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፎች እንዲደርሳቸው ለማስቻል የተከናወኑ ተግበራትን ያደነቁት ብሊንከን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ያልተቋረጠ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ በግጭት ለተጎዱ ወገኖች እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

አሜሪካም በዚህ ሂደት ውስጥ ድጋፉን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን መግለጻቸውን ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ቢሮ ያገኘውን መግለጫ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሁሉን ዐቀፍ ሰላም እንዲመጣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተወሰዱ እርምጃዎችን ያደነቀው መግለጫው በትግራይ ክልል ነገሮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ጥረቶች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።

አንድነቷ፣ ሉዓላዊነቷና እድገቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ለሚከናወኑ ተግባራት አሜሪካ ድገፏን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም መግለጫው አመልክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW