አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና የሚቃወም ሰልፍ በሚኒሶታ ግዛት ዛሬ ይካሄዳል

ኅዳር 21/2014 (ዋልታ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በሚኒሶታ ግዛት ዛሬ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ሰላማዊ ሰልፉ በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰልፉ የተዘጋጀው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በሚኒሶታ ግዛት የሚያደርጉትን የስራ ጉብኝት ተከትሎ ሲሆን ሰልፈኞቹ የባይደን አስተዳዳር በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን የተሳሳተ ፖሊሲና አድሏዊ አቋም እንደማይቀበሉና አካሄዱን እንዲያስተካከል ጥሪ ያቀርባሉ ነው የተባለው።

በሰልፉ ላይ በሚኒሶታ ግዛት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የሚኒሶታ ግዛት በአሜሪካ በርካታ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከሚኖርባቸው ግዛቶች በዋንኛነት የምትጠቀስ ናት።

በተያያዘ ዜና የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጨውን ሀሰተኛ ዘገባ የሚቃወም ሰልፍ አትላንታ በሚገኘው የተቋሙ ቢሮ ፊት ለፊት ነገ እንደሚካሄድም ተመላክቷል።

ከምሽቱ 12 ሰአት ጀምሮ በሚካሄደው ሰልፍ ላይ ሲኤንኤን ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚሰራቸውን ሐሰተኛ ዘገባዎች ማቆም እንዳለበትና ሙያዊ ሥነ ምግባር ተከትሎ እንዲሰራ በሰልፈኞቹ ጥሪ እንደሚቀርብ ተገልጿል።

በሚኒሶታና በአትላንታ ከተሞች የሚካሄዱት ሰልፎች የበቃ ‘#NoMore’ ዘመቻ አካል ናቸውም ተብሏል።