አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችበትን ውሳኔ ልታጤነው ይገባል – የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

ታኅሣሥ 18/2014 (ዋልታ) አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችብትን ውሳኔ አጥብቃ ልታጤነው እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመለከተ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ሥርዓት ያስወጣችብትን ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

የአፍሪካ ሀገራትን በንግድና ሥራ እድል ተጠቃሚ ከሚያደርገው የአጎዋ ንግድ ሥርዓት አሜሪካ ኢትዮጵያን ማስወጣቷ የኢትዮጵያን መንግስት እንዳሳዘነው መግለጫው አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን፣ ፖለቲካዊ መግባታትና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን ባለፉት ሦስት ዓመታት ማከናወኑን ያመለከተው መግለጫው በተለይ ደግሞ የሁለቱን አገራት ረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ያማከለ የለውጥ ሥራዎች ማከወኑንም አንስቷል።

ከአሜሪካ ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር ደግሞ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ግንኙነቱን ለማጠንከር እየተሰራ መሆኑን ያብራራው መግለጫው ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማስወጣት በአጎዋ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ ተግባር ከመሆን ባለፈ በእነሱ ስር ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችንም ኑሮ የሚያመሳቅል መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችበትን ውሳኔ አጥብቃ ልታጤነው እንደሚገባ መጠየቁን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።