አሜሪካን ልዑኳን እስከመላክ ያደረሳት ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ከምትሰጠው ግምት የተነሳ ነው- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – አሜሪካ በፕሬዚዳንት ጆባይደን ልዩ መልዕክተኛዋ የተመራ ልዑካን እስከመላክ ያደረሳት ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ከምትሰጠው በጎ ግምት የተነሳ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

በሴናተር ክሪስ ኩንስ ከተመራው የአሜሪካ ልዑካን ጋር የተደረጉ ውይይት ገንቢ እና ውጤታማ እንደነበር አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት መልካም ግንኙነት ምክንያት ስለወቅታዊው የሀገሪቷ ሁኔታ ለመረዳት ልዑካን እስከመላክ ደርሳለች።

በሀገራቱ መካከል ላለው የቆየ ግንኙነት ትኩረት ባይሰጡ በሴናተር ክሪስ ኩንስ ከሚመራው ልዑክ የመላክ ፍላጎትም አይኖራቸውም ነበር ያሉት አምባሳደር ዲና፣ በኢትዮጵያ ስላሉ ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፍጥነት ልዑካቸውን መላካቸውም ስለሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ ማሰባቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡

የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸው ለሁለቱም ሀገራት ጠቀሜታ ያለው ነውና አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማበላሸት እንደማትፈልግ እኛም እናስባለን ሲሉ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናም ሆነ በአህጉሪቷ ውስጥ ጎላ ያለ ሚና ያላት ሀገር እንደሆነች የገለጹት አምባሳደር ዲና፣ በጸረ ሽብር ትግሉም ሆነ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እንዳላት አስታውሰዋል።

ቀጣናው ግርግር የሚበዛበት እና በሽብር የታወቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ሰላምን የማምጣት እርምጃዎች ወሳኝ መሆናቸውን አሜሪካኖቹም ይረዱታል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልዩ መልዕክተኛ ሴናተር ክሪስ ኩንስ የተመራው ልዑክ የመጣው በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ይበልጥ ቀረብ ብሎ ለመረዳት ያለመ ነው ብለዋል። በመሆኑም በኢትዮጵያ በኩል ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በተለይም በትግራይ ክልል ስለተከናወነው የህግ ማስከበር ጉዳይ ግልጽ እና ዝርዝር ማብራሪያ ለልዑኩ ተሰጥቷል።

በትግራይ ክልል የተካሄደው ዘመቻ መነሻውን፣ ሂደቱን እና አሁን ላይ ምን ደረጃ እንደደረሰ እንዲሁም አካባቢው ላይ ስላለው የመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ እርዳታ በተመለከተ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልዑክ ሰፊ ማብራሪያ መቅረቡን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

በአሜሪካ በኩል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማያስፈልግ በውይይቱ ወቅት መገለጹን የተናገሩት አምባሳደር ዲና፣ ከዚህ ቀደም አሜሪካ ከአንድም ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያን የጸጥታ ሁኔታ መዋቅሮች በክልል ለይቶ የማቅረብ ሁኔታዋ ጣልቃ ገብነት እንደነበር በግልጽ ተነግሯቸዋል፤ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዲረዱ የሚያስችል ትንተና ቀርቦላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ሴናተር ክሪስ ኩንስ እና ልዑካቸውም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በቅርበት መረዳታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ገልጸዋል።

ውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ በኩል የተነሱ ጉዳዮችን ሁሉ በጽሞና በማዳመጥ ሁኔታውን ለመረዳት ጥረት ማድረጋቸውን እንደታዘቡ ተናግረዋል።

ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልዑክ ጋር በቂ የሆነ የመልዕክት ልውውጥ የተደረገበት እና ውጤታማ ውይይት የተደረገበት መድረክ ተፈጥሯል ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ልዑካኑ ወደ ሀገራቸው ከሄዱ በኋላ የሚገልጹትን ነገር ካሁኑ መተንበይ ባይቻልም፤ ሴናተር ክሪስ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ቁልፍ አጋር መሆኗን አስታውቀው፣ በሀገሪቱ የሚደረግ ማንኛውም አሉታዊ ጉዳይ አሜሪካንን እንደሚያሳስባት መናገራቸውን አስታውሰዋል።

አምባሳደር ዲና እንዳስታወቁት፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው በጎ ግምት እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሀገሪቷ ከተሞች ሰልፍ በመውጣት እና ተቃውሟቸውን በተለያየ መንገድ በማቅረብ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግሥት እውነተኛ አካሄድ ቀርቦ እንዲመለከት ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያደረጉት ጥረት የአሜሪካው ልዑክ በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን ይታመናል።