አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከተለያዩ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ጋር መከሩ

ሐምሌ 23/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ፒኤችዲ) ከተለያዩ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ጋር መምከራቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
አምባሳደሩ ባለፉት ቀናት ከሴናተር ቴድ ክሩዝ፣ ከኮንግረስ አባሎቹ ቻክ ፍሌይሽማን፣ ጁሊያ ሌትሎው፣ ዳሬል ኢሳ፣ ክሪስ ስሚዝ እና ስቲቭ ዎማክ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደሩ ከባለሥልጣናቱ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ አካባቢዎች እያደረገ ስላለው ሰብአዊ ድጋፍ፣ ስለሰላም ግንባታ፣ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን የማስረፅ ሂደት፣ በቅርቡ አሸባሪው አልሸባብ ኢትዮጵያን ለመተንኮስ ስለመመኮሩ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን ኤምባሲው ገልጿል።
ኢትዮጵያ በHR.6600 እና S.3199 ረቂቅ ሕጎች ላይ ስላላት ስጋትም ያነሡ ሲሆን፣ እነዚህ ረቂቅ ሕጎች የሚፀድቁ ከሆነ ረጅም ዘመናትን በዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እና በኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ባሉ መልካም ጅማሮዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠር ውጪ ምንም አዎንታዊ ውጤት እንደማያመጡ አብራርተውላቸዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከአጎዋ ስምምት ተጠቃሚ እንዳትሆን መደረጉ ለፍተው የሚያድሩ ኢትዮጵያውያንን እየጎዳ በመሆኑ ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ዳግም እንድትመለስ ጥረት እንዲያደርጉ ለባለሥልጣናቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ በሰላም ግንባታ ጥረቶች እና የሰላም ውይይት ላይ አዎንታዊ እመርታ እያሳየ ስለመሆኑ እማኝነታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራቱ መካከል እየተስተዋለ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንደሚሠሩ መናገራቸውን ኤምባሲው ገልጿል።