አረንጓዴ ዐሻራ በትልቁ አስበን ከተባበርን በትልቁ ማሳካት እንደምንችል ምስክር ሆኖናል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ነሐሴ 8/2014 (ዋልታ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር መጀመር በትልቁ አስበን ከተባበርን በትልቁ ማሳካት እንደምንችል ምስክር ሆኖናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

በሀገራችን አረንጓዴ ዐሻራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ እድሎችን ፈጥሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አንደኛ በትልቁ አስበን ከተባበርን በትልቁ ማሳካት እንደምንችል ምስክር ሆኖናል ብለዋል።

በጥቂት ሚሊየኖች ችግኝ መትከልን እንደ ድል በምትቆጥር ዓለም ላይ በአራት ክረምት 25 ቢሊየኖች ማሳካት እንደሚቻል አሳይተንበታልም ነው ያሉት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁለተኛው ለብልጽግና መሠረት የሚሆን ባህል መፍጠሩ ነው ያሉ ሲሆን ችግኝ የመትከል ባህል ሲውል ሲያድር በምግብ ራሳችንን እንድንችል፣ ግድቦቻች ዘላቂ ዝናብ እንዲያገኙ፣ ለም አፈራችን እንዳይሸረሸር በማድረግ በድርቅና በርሃብ የጠለሸ የሀገራችን ስም እንዲታደስ በር ይከፍታል ብለዋል።