መስከረም 18/2015 (ዋልታ) በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አራቱም የዩክሬን አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸው ተገለጸ።
በአካባቢዎቹ ከመስከረም 13 ጀምሮ ህዝበ ውሳኔ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በህዝበ ውሳኔው 96 በመቶ ድምጽ ሰጪዎች ሩሲያን መቀላቀልን መርጠዋል፡፡
በዩክሬን እንዲሁም በበርካታ የምዕራባውያን ሀገራት ውግዘት የደረሰበት ህዝብ ውሳኔ ከመስከረም 13 እስከ መስከረም 17 ድረስ ተካሂዷል።
ህዝበ ውሳኔው የተካሄደው በአራት የዩክሬን ግዛቶች ላይ ሲሆን ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች ያካተተ ነበር ተብሏል።
ህዝበ ወሳኔው መጠናቀቁን ተከትሎ የሞስኮ ደጋፊ ባለስልጣናት በትናትናው እለት ድምጽ መስጠት ሂደት መጠናቀቁን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው አራቱም አካባቢዎች የሚገኙ ዩክሬናውያን ሩሲያን ለመቀላቀል ድምጽ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
የህዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ መጠናቀቁን ተከትሎ በተካሄደው ቆጠራም 96 በመቶ ዩክሬናውያን ሩሲያን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
ሞስኮ በዩክሬን ግዛቶች ላይ የምታካሂደው ህዝበ ውሳኔ በዩክሬንና ምዕራባውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የሚታወቅ ነው።
ኪቭ ባለስልጣናት ህዝበ ውሳኔው ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ ሲገልጹ መቆየታቸውም ይታወቃል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ምርጫውን “የይስሙላ ድምጽ” ሲሉ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ “አሳፋሪ” ነው ሲሉ ገልጸውታል። አሜሪካ በበኩሏ ህዝበ ውሳኔው “የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርሆዎችን የሚጥስ ነው” ብለዋለች።
ሩሲያ በበኩሏ ሞስኮ፤ በሩሲያ ኃይሎች ስር የሚገኙትን የዶንባስ ግዛቶችን ለመከላከል ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ጦር ማሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ማስጠንቀቋን የአልዐይን ዘገባ አስታውሷል።
የቀድሞ የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው የዶንባስ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም አደጋ ለመከላከል፤ አስፈላጊ ነው የሚባለው የትኛውም የጦር መሳሪያ በጥቅም ላይ ታውላለች ማለታቸው አይዘነጋም።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW