አራት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ወድቆ ያገኙትን 3 ሺሕ 900 ዶላር አስረከቡ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) በታማኝነት እና በቅንነት ማገልገል ከሕዝብ እና ከመንግሥት የተሰጠን አደራ ነው ያሉት አራት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ወድቆ ያገኙትን 3 ሺሕ 900 የአሜሪካ ዶላር ማስረከባቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ምክትል ኢንስፔክተር ዘነበ እሸቱ፣ ምክትል ኢንስፔክተር ዳግም ግርማ እና ዋና ሳጅን ዓለምነሽ ግርማ የተባሉ የአቃቂ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባላት በጥበቃ ሥራ ላይ እያሉ ቆሻሻ ፌስታል ውስጥ የተጠቀለለ 1 ሺሕ 900 የአሜሪካ ዶላር አግኝተው ለጣቢያው አስረክበዋል።

በተመሳሳይም ምክትል ሳጅን ብርቱ ሙዳ በፖሊስ ጣቢያው አካባቢ ስትንቀሳቀስ በማስክ የተጠቀለለ 2 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር በማግኘቷ ወዲያውኑ ለፖሊስ ጣቢያው ማስረከቧ ተገልጿል።

የፖሊስ አባላቱ በሠሩት አርዓያነት ያለው ተግባር ታላቅ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ተግባራቸውን አጠናክረው ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የቆሙለት ዓላማ የገባቸው እና የመለዮን ክብር የተረዱ አባላት በሚሠሩት መልካም ተግባር ኅብረተሰቡ ከሚሰጣቸው ክብር በሻገር የተቋሙ ግርማ ሞገሶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

በመልካም ሥነ ምግባር እና አገልግሎት ዕውቅና ሊሰጣቸው የሚገባቸውን አመራር እና አባላትን ማበረታታት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡