አስገዳጅ የጥራት ደረጃን ያላሟሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ታገዱ

ጥር 20/2014 (ዋልታ) በገቢ ምርቶች ላይ በተደረገ የላብራቶሪ እና የኢንስፔክሽን ፍተሻ ከኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ እንዳይገቡ መታገዳቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተደረገ የላብራቶሪ እና የኢንስፔክሽን ፍተሻ 3 ነጥብ 5 ሜ.ቶ ኤል ኢ.ዲ አምፖል፣ 25 ነጥብ 8 የኤሌክትሪክ ማከፋፋያ፣ 368 ካርቶን ወይም 368 ሺሕ 800 ፍሬ መጠን ያለው የኃይል አባካኝ  አንፖል፣ 4 ሺሕ 800 ፍሬ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ 8.131 ሜ.ቶን የአርማታ ብረት እና 12.6 ሜ.ቶ ጥቅል ቆርቆሮ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጋቸው ታውቋል፡፡

በተጨማሪም 5 ሺሕ ፍሬ የፍሎረሰንት አምፖል፣ 293 ካርቶን የኤሌክትሪክ ሶኬት ማከፋፋያ፣ 55.3 ሜ.ቶን የአተር ክክ፣ 24.93 ሜ.ቶ ሩዝ፣ 693.8 ቶን ቀይ ሽንኩርት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡና የኅብረተሰቡን ጤና፣ ደኅንነትና ጥቅም እንዳይጎዱ መደረጉን በሚኒስቴሩ የዘርፉ ዳይሬክተር እያሱ ስምዖን መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡