መስከረም 12/2015 (ዋልታ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን በወረራ በቆየበት ጊዜ ከ128 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ዘረፋ እና ውድመት ቢፈጽምም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጠያቂ አለመደረጉ መላውን ሕዝብ አሳዝኗል ሲል የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን አሸባሪው ህወሓት በዞኑ በወረራ በቆየበት ወቅት ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል ብለዋል።
“ንጹሃንን በግፍ ጨፍጭፏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ የሚችለውን ንብረት ዘርፏል፣ ያልቻለውን ደግሞ ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጥ በማድረግ አውድሟል” ብለዋል።
ቡድኑ በመንግሥት እና በሕዝብ መገልገያ ተቋማት እና ንብረቶች ላይ ያደረሰው ዝርፊያ እና ውድመት 104 ቢሊዮን ብር ግምት እንዳለው እና ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ደግሞ የግለሰቦች ንብረት ላይ የተፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል።
ቡድኑ በዞኑ 242 የጤና፣ 230 የትምህርት፣ 87 የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ 109 ኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የክልሉ መንግሥት እና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ በጋራ ባስጠኑት ጥናት መረጋገጡን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
“ደሴ እና ኮምበልቻ በክልሉ ከፍተኛ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመትን ከተሞች በመሆናቸው በአማራ ክልል ከደረሰው አጠቃላይ ውድመት 45 በመቶ በደቡብ ወሎ የደረሰ መሆኑን በጥናቱ ተረጋግጧል” ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ለመግለጽ የሚዘገንን እና አስነዋሪ ግፍ እና በደል በሕዝብ ላይ ቢፈጽምም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጠያቂ አለመደረጉ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ያሳዘነ እና ያስቆጣ መሆኑን አመልክተዋል።
አሁንም የዓለም ሕዝብ እና ተቋማት በሐሰተኛ መረጃ ከመንጠልጠል ይልቅ መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ እና ሐቅ ተገንዝበው የሽብር ቡድኑን በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕን ሊያሰፍኑ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቡድኑ የአርሶ አደሩን የእርሻ በሬ ጭምር አርዶ ከመብላት ባለፈ በጥይት ጨፍጭፎ በእንሰሳት ላይም ግፍ የፈጸመ አረመኔ መሆኑን ጠቁመው የኅብረተሰቡን ቀለብ ሽሮ እና በርበሬ ሳይቀር የዘረፈ ነውረኛ ቡድን መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በዞኑ ከ2ሺሕ 600 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች ላይም በከባድ መሳሪያ ጭምር ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ 617 ቤቶችን ከእነ ሙሉ ንብረታቸው ማውደሙንም አመልክተዋል።