አሸባሪው ህወሓት በኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ ጭፍጨፋ እየፈጸመ መሆኑን ኤርትራ አስታወቀች

ኤርትራዊያን ስደተኞች

ሐምሌ 05/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓት በኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የበቀል እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኤርትራው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስታወቁ።

ህወሓት በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ ባሉ ንጹሃን ኤርትራዊያን ላይ ሳይቀር በበቀል ተነሳስቶ ጭፍጨፋ እየፈጸመ እንደሚገኝ ነው አቶ የማነ የገለጹት።

ህወሓት እየፈጸመ ያለው የበቀል ግድያና ጭፍጨፋ ብሎም የድርጅቱ ህገ ወጥ ተግባራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር ባሉ ኤጀንሲዎች እና የድርጅቱ አፍቃሪ መገናኛ ብዙኃን ቸል መባሉን ገልጸዋል።

በጄኔቫ የኤርትራ ኤንባሲ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም ትግራይ ክልል ባሉ የስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ንጹሃን ኤርትራዊያን እየተገደሉ ይገኛሉ።

በጄኔቫ ያሉት የኤርትራ አምባሳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር መነጋገራቸውን ኤንባሲው አስታውቋል።

ከዚህ መረጃ በፊትም አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ መሰረት በትግራይ ክልል ያሉ ንጹሃን ዜጎች የደህንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ጠቅሶ ስጋቱን ማስተወቁ አይዘነጋም።

በተመሳሳይም ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን የጤና ተቋማት መዘረፋቸውንና ንጹሀን ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት መጋለጣቸውን ማስታወቁ እንዲሁም ከሳምንት በፊት በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎት መስጠት ማቆሙን መግለጹ ይታወሳል።