አሸባሪው ሕወሓት ወደ ሠላም ንግግር እንዲመጣ የትግራይ ሕዝብ ጫና እንዲያደርግ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) የትግራይ ሕዝብና የትግራይ ወዳጆች አሸባሪው ሕወሓት የጀመረውን ጦርነት በአስቸኳይ አቁሞ ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጣ ጫና እንዲያደርጉ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሚኒስትሩ በትግራይ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ምሁራን ፣ ዳያስፖራዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ስለ ሠላም እንዲዘምሩና ሕወሓት ጦርነት አቁሞ ወደ ሠላማዊ ውይይት እንዲመጣ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የትግራይ ጉዳይ በዘላቂነትና ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ ዕልባት ማግኘት የሚችለውም በውይይትና በሠላማዊ መንገድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የሀገሩ ተስፋና የሕዝቡ መሪ መሆን የሚችለው ወጣቱ ትውልድ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ኪሳራ ያጋጠማቸውን ዕድሜያቸውን የጨረሱ ግለሰቦች መንበረ-ሥልጣን ለማራዘም ሲባል ወደ ተከታታይና ትርጉም የለሽ ጦርነት መማገድ እና ሕይወቱ መቀጠፍ የለበትም ነው ያሉት፡፡

ሁሉም የትግራይ ተቆርቋሪ፣ ሕወሓት የሚሰጣቸውን አጀንዳ ወደጎን በመተው፣ አጀንዳቸውን ሕዝብ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡