አሸባሪው ሕወሓትን የሚያወግዝ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው

መስከረም 6/2015 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሰልፍ የፊታችን እሁድ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

ዋይት ሐውስ ፊት ለፊት የሚከናወነው ሰላማዊ ሰልፍ የተለያዩ አላማዎችን ያነገበ መሆኑን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ጣሰው መላከሕይወት ገልጸዋል።

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ዳግም ወረራ እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

ከሰላማዊ ሰልፉ በተጨማሪ በአሜሪካ የሚገኙ የሲቪክ ተቋማትና ጥምረቶች የሀገሪቷ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሚዛናዊ እይታ እንዲኖራቸው የማወያየትና የማስረዳት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያን የሚደግፉ የትዊተር ዘመቻዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ ኤርትራዊያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን ሰልፍ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት፣ ከተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳጆች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል።