አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ 1.3 ቢሊየን ብር የሚያወጣ ንብረት ማውደሙ ተገለፀ

ታኅሣሥ 17/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ብቻ ወደ 1.3 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የግልና የመንግስት ንብረት ማውደሙ ተገለፀ፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ሰለሞን ታምሩ እንደገለፁት አሸባሪው የሸኔ ቡድን በተንቀሳቀሰባቸው የምዕራብ ወለጋ ዞን አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል፡፡
ቡድኑ ባለፉት 2 ዓመታት አርሶ አደሮችን ምግብ አምጡ እያለ ሲያስገድድ የነበረ ሲሆን ለእኩይ ዓላማው ባልተባበሩ የዞኑ ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ሲፈፅም እንደነበረ ገልፀዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኞችን፣ ኢንቨስተሮችን፣ ተቋራጮችን፣ ያለ ክፍያ የሚሰሩ ሚሊሻዎችን፣ አርሶ አደሮችን እና የሃይማኖት አባቶችን ኢላማ ያደረገ አሰቃቂ ግድያ በፅንፈኛውና አሸባሪው ሸኔ መፈፀሙንም ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ወደ 790 የሚደርሱ የዞኑ ነዋሪዎች በአሸባሪው ሸኔ አሰቃቂ ግድያ የተፈፀመባቸው ሲሆን ከዚህ ወስጥ ወደ 301 የሚሆኑት አርሶ አደሮች መሆናቸው ቡድኑ ፀረ-ሕዝብ መሆኑን ያሳየበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደዚሁም ቡድኑ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በመሆን ኦሮሚያን፤ አልፎም ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ያነሱት የዞኑ አስተዳዳሪ ሰለሞን ታምሩ በዚህም ወደ 1.3 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የግልና የመንስት ሀብት አውድሟል ብለዋል፡፡
በዞኑ ከሚገኙ 452 የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ማለትም ወደ 226 የሚደርሱ የቀበሌ አስተዳደሮችን ሙሉ በሙሉ ዘርፎ፤ አይጠቅመኝም ያለውን አቃጥሎና አውድሞ መፈርጠጡን ነው የገለፁት።
የዞኑ ነዋሪዎች በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሆኔታ ውስጥ ሆነው አሸባሪውን ሸኔ ለማጥፋት ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረ ተናግረው ሸኔን ከክልሉ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ከ4 ሺሕ በላይ የዞኑ ወጣቶች በፍቃዳቸው መከላከያን ተቀላቅለዋል፡፡
ሕዝቡ ከመቀነቱ እየፈታ ከ190 ሚሊየን በላይ ገንዘብ 5 ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በማሰባሰብ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጉ፤ የወለጋ ሕዝብ ኢትዮጵያን የሚወድና ለሀገሩ ተቆርቋሪ የሆነ አሸባሪውን ሸኔን አምርሮ እንደሚጠላ፤ በነቂስ ወጥቶ በምርጫ ካርድ ለመረጠው መንግስት ጎን ተሰልፎ ጠላትን እየታገለ ስለመሆኑ ማሳያ ነውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ከሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሆንም እየተሰራ ባለ ኦፕሬሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የሸኔ አባላትን ብለው ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ ወደ 1ሺሕ 187 ተገድለዋል ነው ያሉት።
እንዲሁም ከ600 በላይ የሚሆኑት እጃቸውን ለአባ ገዳ፣ ለሀገር ሽማግሌ እና ለፀጥታ ኃይሉ እየሰጡ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
በደረሰ አማረ