አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞና አማራ ህዝቦችን በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት መቼም አይሳካለትም – ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት መቼም አይሳካለትም ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ የክልሉን የ2014 ዓ/ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሁኔታን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም በክልሉ ከፍተኛ ሥራ አፈጻጸም ቢኖርም እንደ አገር እና እንደ ክልል የገጠሙ 5 ትልልቅ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

እነዚህም ጦርነት፣ ድርቅ፣ ኮቪድ፣ ዓለም ዐቀፍ ሁኔታዎች እንዲሁም የሸኔ የሽብር ቡድን ያደረሳቸው ጥፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው የሸኔ ቡድን ዜጎችን በጅምላ መግደል፣ መዝረፍና ማሰቃየትን ጨምሮ አስነዋሪ ድርጊቶችን ሲፈጽም መቆቱን ገልጸዋል፡፡

ሸኔ የራሱ የሆነ ሀሳብ የሌለው፣ ለሌሎች ኃይሎች ተላላኪ የሆነና እኩይ ሀሳቡን በጉልበት ሕዝብ ላይ ለመጫን የሚፈልግ ቡድን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያስረዳው አጀንዳ የሌለው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ አረመኔነቱን ያስመሰከረበትን ተግባር በሕዝብ ላይ እየፈጸመ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህ አሸባሪ ቡድን ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ዙሪያ በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡

ቡድኑ በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት ወንድማማች የሆኑ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦችን ለማጋጨት በማሰብ ቢሆንም ይህ መቼም አይሳካለትም ብለዋል፡፡

የሁለቱን ክልል ህዝቦች በማጋጨትም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማ አድርጎ ቢንቀሳቀስም የሕዝቹን አንድነት እና አብሮ የመኖር እሴት ግን ማንም ሊያጠፋው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ አካላት ጠንካራ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሣራ እየደረሰ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም ቡድኑን ለማጥፋትና ሕዝቡ ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ለማስቆም ከሕዝቡ ጋር በመሆን የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ፣ የሕዝቡ ተጠቃሚነት ተረጋግጦ እንዲቀጥል የተጀመረው አሸባሪው ሸኔን የማጥፋት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡