አሸባሪው የህወሓት ቡድን ንፁሃን ዜጎችን ስለመረሸን

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ንፁሃን ዜጎችን መንገድ ላይ አሰልፎ መረሸኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው ህወሓት በጭና ቀበሌ ንፁሃንን በግፍ መጨፍጨፉን፤ የ6 ወር ህፃን ልጅ በእናቷ ጀርባ እንደታዘለች መግደሉን ተናግረዋል።

ቡድኑ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባት እና ደባርቅ ወረዳን ለመቁረጥ ያደረገው ሙከራ በአገር መከላከያ ሠራዊትና በፀጥታ ሃይሎች ጀግንነት ከሽፎ ሽንፈት ሲደርስበት በአካባቢው ያገኛቸው ንፁሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ አድርሶ መሄዱ ተገልጿል፡፡

በጅምላ በግፍ የገደላቸው በርካታ ንፁሃን ዜጎች አስከሬንም በጭና ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተቀብሯል ነው የተባለው።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት እና በፀጥታ ኃይሎች ሽንፈት ሲደርስበት በቀበሌው የሚገኙ ንፁሃን ዜጎችን ገድሎ መሸሹን ተናግረዋል።

የዓይን እማኞቹ እንደተናገሩት አሸባሪው ቡድን ንፁሃንን መንገድ ላይ አሰልፎ ነው የረሸናቸው።

ቡድኑ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህፃናትን እና ታመው ቤት የዋሉ ንፁሃንን መግደሉን እንዲሁም የአንድ ቤተሰብ ስድስት አባላትን በግፍ መግደሉንም ነዋሪዎች ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡