አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚያወጣ መድኃኒት ዘረፈ

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚያወጣ መድኃኒት ዘረፋ ፈፀመ።

በሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ደሴ ቅርጫፍ ዘረፋና ውድመት ማድረሱ ነው የተገለጸው፡፡

የደሴ መድኃኒት አቅርቦት ቅርጫፍ በምስራቅ አማራ የሚገኙ 6 ዞኖችና  ከፊል አፋርን  ጨምሮ 29 ሆስፒታሎች 318 የጤና ጣቢያዎች የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል።

የሽብር ቡድኑ ያወደመው የኤጄንሲ ቅርንጫፉ ከመንግስት ጤና ተቋማት በተጨማሪ የቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች፣ የማረሚያ ቤቶች፣ ከ45 በላይ የግል ጤና ተቋማቶች፣ ከ100 በላይ የግል መድኃኒት ቤቶች የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት የሚያሟላ እንደነበርም ተመላክቷል፡፡ ።

የሽብር ቡድኑ በመድኃኒት ማከማቻው ውስጥ የሚገኘውን የክትባት ማከማቻና ማቀዝቀዣ መጋዘን በመስበር ከህፃናት ክትባት እስከ ኮቪድ-19 ክትባት ድረስ ዘርፏል የማይፈልገውን ከጥቅም ውጭ አድርጎታል፤ ይህንንም ዋልታ ቴሌቪዥን በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል።

የምስራቅ አማራ ማኅበረሰብ በተላላፊ በሽታ እንዲጠቃና የተራዘመ የጤና ቀውስ እንዲገጥመው በማሰብ ህፃናት ለፖሊዮና ለልምሻ በሽታ እንዲዳረጉ አስቦ ተቋሙን ማውደሙ ነው የተገለጸው።

ዋልታ ቴሌቪዥን ጢጣ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመገኘት በደሴ የመድኃኒት አቅርቦት ቅርጫፍ ምልከታ ባደረገበት የመድኃኒት መደርደሪያዎች ባዶ መሆናቸውን፣ የተለያዩ መድኃኒቶች መሬት ላይ መበተናቸውንና የክትባት ማከማቻና ማቀዝቀዣዎች ተሰብረው የክትባት ብልቃጦች ተበታትነው ተመልክቷል።

በምንይሉ ደስይበለው (ከግንባር)