አሸባሪውን የሸኔ ቡድን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ታኅሣሥ 6/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።

ከሚዳ ቀኝ ወረዳ እስከ ኬኒያ ድረስ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏቸው አሸባሪውን ሸኔ ቡድን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ ነው የገለፀው።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት አንደኛ ተጠርጣሪ አሚር አማን የአሶሺዬትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ፣ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ቶማስ እንግዳ የካሜራ ባለሙያ እና ሦስተኛ ተጠርጣሪ አዲሱ ሙሉነህ የኤፍቢሲ ጋዜጠኛ መሆናቸው ተገልጿል።

ጋዜጠኞቹ የሽብርተኛውን ሸኔ ቡድን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከታትሎ በመቅረጽና ቃለ መጠይቅ በማድረግ መረጃዎችን በማሰባሰብ ኬንያ ለሚገኘው እና የአሶሽዬትድ ፕሬስ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ለሆነው ግብጻዊው ካሊድ ካዚሃ መላካቸው በማስረጃ መረጋገጡን ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከአዲስ አበባ በመንቀሳቀስና የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ቀርጸው እንዲመጡ ከግብጻዊው ጋዜጠኛ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ጉዳዩ ዓለም ዐቀፍ በሆነው አሶሽዬትድ ፕሬስ እንዲተላለፍ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።

ወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበትና የተለያዩ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በወቅቱ አዲስ አበባ ተከባለች፤ ሕወሓትና ሸኔ ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፤ በሚል ወሬ የሚያናፍሱበትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአገር ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ወደ ግንባር በዘመቱበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ ሆን ብለውና አስበውበት ሕዝቡን ለማሸበር ቀረጻው በዓለም ዐቀፍ ሚዲያ እንዲተላለፍ በማድረጋቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አሸባሪው ቡድን እንዲታወቅ የሚዲያ ተልዕኮ ተቀብለው ኅዳር 16 ቀን ወደ ስፍራው በማቅናት እስከ ኅዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ቀረጻ በማከናወን እና ፕሮዳክሽን በመስራት ከላኩ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው እና በስራ ገበታቸው ኅዳር 19 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በወቅቱም በእጃቸው ከተገኙት ላፕቶፕ እና ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይም በርካታ ማስረጃዎች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።

ጋዜጠኞቹ ረጅም ርቀት ተጉዘው ያደረጉት ቀረጻ በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ ይነዛ የነበረውን ፕሮፖጋንዳ ለመደገፍ ሆን ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑም ነው የተገለፀው።