ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል መንግሥት ያወጀውን የክተት ጥሪ በሙሉ ልብ የሚቀበለው መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ፡፡
“የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር ሉዓላዊነትና አንድነትን ለማስጠበቅ፣ ሕግና ስርዓትን ለማስፈንና አገርን ለማዳን የጀመረውን ጥረትና የክልል መንግሥታት እያደረጉት ያለውን ቁርጠኝነት የተሞላበት የተባበረ እንቅስቃሴ ንቅናቄያችን በአክብሮት ይመለከተዋል” ብሏል አብን ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መልዕክት።
ለክተት ጥሪው ተግባራዊነት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ የገለፀው ፓርቲው የክልሉ መንግስት የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቋል።
መላው የድርጅቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች እና ህዝቡም ጥሪውን ተቀብሎ የክተት ዘመቻውን እንዲቀላቀል አሳስቧል።