አትሌት ሻለቃ ኃይሌ በግንባር መሰለፍን ጨምሮ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ አለ

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) “በግንባር መሰለፍን ጨምሮ ለኅልውና ዘመቻው የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ፡፡
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ በኢትዮጵያ የተደቀነው አደጋ አፍሪካን የማንበርከክ ዓላማን ያነገበ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሙከራ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት መሆኗን ለኢዜአ ገለፆ ኢትዮጵያን በማንበርከክ የጥቁር ሕዝቦችን አኩሪ ታሪክ ለመቀማት የተቀናጀ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ክብር ወደ ግንባር መዝመታቸው አገሩን ከሚወድ መሪ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተል ጥሪ አቅርቧል።
መላ አፍሪካዊያን ትግሉ የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን በመገንዘብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአንድ ወቅት የጎበኛት የጎብኚዎች መናኸሪያ የነበረችውን የሶሪያዋ አሌፖ ከተማ በምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት ምክንያት ወደ ፍርስራሽነት መቀየሯን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያዊያን በግንባር ከመዝመት ባሻገር በደጀንነትም በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝቧል።