አቶ ደመቀ መኮንን ከህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የስልክ ውይይት አደረጉ

ነሃሴ 21/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሱብራማንያ ጄይሻንካር ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል።

አቶ ደመቀ በውይይታቸው ህንድ በዓለም አቀፍ መድረክ ለኢትዮጵያ እየሰጠች ላለው መርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይ  በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚፈልጉ አካላት ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገውን  አካሄድ በመቃወም ህንድ ለኢትዮጵያ ድጋፍ መስጠቷ የሚመሰገን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ህንድ በተመለከተ በምታራምደው ፍትሃዊ አቋምም ያመሰገኑት አቶ ደመቀ፥በቅርቡም በቱኒዚያ በኩል ለፀጥታው ምክር ቤት በድጋሚ ሊቀርብ የታሰበው ኢ-ፍትሃዊ የውሳኔ ሀሣብ ሶስቱ ሀገራት ከተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚፃረር መሆኑን አውስተዋል።

ከዚህ አንጻርም ይህንን አካሄድ ለማስቆም ህንድ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በህወሓት የሽብር ቡድን ቆስቋሽነት የተፈጠረውን ሁኔታን በተመለከተም ለህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለፃ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዜጎች በማሰብ የተናጥል የተኩስ ማቆም ቢያደርግም የሽብር ቡድኑ ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች ማስፋቱን፣ ሕፃናትን ጭምር ለውጊያ እያሰለፈ  እንደሚገኝና ሲቪሎችንም የጥቃት ዒላማ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም የህወሓት የሽብር ቡድን እያደረገ ያለውን ህጻናትን ለውጊያ የማሰለፍና ሲቪሎችን ዒላማ የማድረግ ዓለም አቀፍ ወንጀልን በጽኑ እንዲኮንኑ ጠይቀዋል።

የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሱብራማንያ ጄይሻንካር በበኩላቸው፥ ህንድ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ የሚደረግን የጣልቃ ገብነት ተግባር እንደምትቃወም እና ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን በራሷ ልትፈታ እንደምትችል ስለምታምን ድጋፏን ለኢትዮጵያ መስጠቷን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ህንድ በሦስቱም ( የላይኛው፣ የመካከለኛው እና የታችናው የተፋስስ ሃገራት)  እንደመሆንዋ መጠን ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን እንደምትደግፍ አመላክተዋል።

የናይል ተፋሰስ ተጋሪ ሀገራት በውይይትና በመግባባት ልዩነቶቻቸውን ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄን መከተላቸው ተገቢ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በውይይቱ ወቅት የሃገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ ንግድና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የበለጠ ለማስፋት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።